የኢትዮጵያ የአጭርና መካከለኛ የሜዳ ላይ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታኅሣሥ 3 ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአጭርና መካከለኛ የሜዳ ላይ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታኅሣሥ 3 ይጀመራል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 27/2016 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ የአጭርና የመካከለኛ የሜዳ ላይ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከታኅሣሥ 3 እስከ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል።
ውድድሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያከናውናቸው ዓመታዊ ውድድሮች አንዱ ሲሆን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይከናወናል።
በዘንድሮው ሻምፒዮናም በድምሩ 19 ክለቦችና ተቋማት የአቋም መለኪያ ለማድረግ በዚህ ውድድር ይሳተፋሉ።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር የሥራ ሂደት ተወካይ የሆኑት ብሥራት ለጥይበሉ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በዘንድሮው ውድድር 770 አትሌቶች ለውድድሩ መመዝገባቸውን ገልፀዋል።
ከነዚህም ውስጥ 451 ወንድ 319ኙ ደግሞ ሴት አትሌቶች እንደሆኑ ተናግረዋል።
በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች የገንዘብ፣ የሜዳልያና የዋንጫ ሽልማት እንደተዘጋጀላቸው ገልፀዋል።
በሁለቱም ፆታዎች 1ኛ ለሚወጡ 3ሺህ ብር፣ 2ኛ ለሚወጡ 2ሺህ ብር፣ 3ኛ ለሚወጡት ደግሞ የ1ሺህ 500 ብር ሽልማት እንደሚበረከትላቸው አስታውቀዋል።
በድብልቅ ሪሌይ ለሚወዳደሩት አትሌቶች ደግሞ በሁለቱም ፆታዎች 1ኛ ለሚወጡት 6ሺህ ብር፣ 2ኛ ለሚወጡት 4 ሺህ ብር፣ 3ኛ ለሚወጡት ደግሞ የ2ሺህ ብር ሽልማት እንደሚሰጣቸው ገልፀዋል።
በውድድሩም 18 ታዋቂ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከወንዶች ኤርምያስ ግርማ ከሲዳማ ቡና ከሴቶች ደግሞ ብርቄ ኃየሎም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአብነት ይጠቀሳሉ።