መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ ሃገራት በሰው ሃብት ልማት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገለጸ

360

አዲስ አበባ ፤ ህዳር27/2016(ኢዜአ)፡- መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ ሃገራት ፈጠራን ማእከል ያደረገ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲያመጡ  በሰው ሃብት ልማት ላይ አተኩረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ።

በአፍሪካ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሃገራት በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ዙሪያ በፖሊሲ አውጭዎች፣ በምሁራን እና የልማት አጋሮች እና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ትብብር በተዘጋጀው የበይነመረብ የውይይት መርሃግብር ላይ እንደተገለጸው የሰለጠነ ሰው ሃብት አቅም በሚፈለገው ደረጃ አለመገኘት እና የመንግስት እዳ መጨመር መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ ሃገራት ዋነኛ ተግዳሮቶች ናቸው ተብሏል።

በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የሰሜን አፍሪካ ዳይሬክተር ዙዛና ብሪክሾቫ ሽዊድሮዊስኪ “ ሃገራት በሰው ሃብት ክህሎት ላይ በትኩረት መስራትና የትምህርት ስርአታቸውን ከጊዜው ጋር ማራመድ አለባቸው” ያሉ ሲሆን “ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ተዋውቆ ምን፣ እንዴት፣ የትና መቼ መስራት እንዳለበት የተገነዘበ ዜጋ የሚፈጥሩ ከሆነ ካሉበት ማነቆ ፈጥነው መውጣት ይችላሉ” ሲሉ መክረዋል።

ወቅቱ የሚጠይቀውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ማቅረብ ያልቻሉት የአፍሪካ ባለ መካከለኛ ገቢ ሃገራት ፈጠራን ማእከል ያደረገ እድገት ለማምጣት እየተቸገሩ መሆኑን ይፋ ያደረገው የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ሃገራቱ የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያስመዘግቡም የሰው ሃብታቸው ላይ ከወዲሁ መስራት አማራጭ የማይገኝለት መፍትሄ ነው ብሏል።

አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት ተቀላቅሎ ባለከፍተኛ ገቢ የመሆን ርእይ ያላቸው ሃገራት መዋቅራዊ ሽግግራቸውን በዘላቂነት ለማሳካት ያግዙናል የሚሏቸውን አዳዲስ ፈጠራዎችና ወቅቱ የሚሰጣቸውን እድሎች አሟጠው መጠቀም እንዳለባቸውም ኮሚሽኑ መክሯል። 

ከሌሎች ሃገራት አንጻር እነዚህ ሃገራት መንግስታዊ የእዳ ጫናቸው እያደገ በመምጣቱ ዘላቂ እድገትና ልማት ማስመዝገብ ብሎም ዘላቂ የልማት ግቦችን በማሳካት የዜጎቻቸውን ህይወት በአስተማማኝ ሁኔታ የመቀየር ጥረታቸው እየተገደበ መሆኑን ያተተው ዘገባው ሃገራቱ አሁን ባለው የገንዘብ ስርአት እምነት እንዲያጡ እያደረጋቸው መሆኑንም አንስቷል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ምሁራን ተመራማሪዎች ፖሊሲ አውጭዎች እና የልማት ባለድርሻዎችን በማካተት ሰፋ ያለ የምክክር ጉባኤ በሞሮኮዋ ማራካሽ ለማድረግ ለሚመጣው የካቲት ቀጠሮ መያዙንም የዥንዋ ዘገባ አመልክቷል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም