የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፡- በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር የሚተዳደሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውጤታማ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የ2016 ዓ.ም ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብዱራህማን ኢድ ጣሂር በዚሁ ጊዜ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማነት ለማሳደግ የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ ከጥቂት የልማት ድርጅቶች ውጪ በርካቶቹ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ትርፋማነታቸውም እየጨመረ መሆኑን አንስተዋል።
ለአብነትም በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በተቋሙ ሥር ያሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 249 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
ከዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከፍተኛውን ገቢ ያስገኙ ተቋማት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተቋማቱን ውጤታማና ትርፋማ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት በቀጣይ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ የልማት ድርጅቶቹ እያከናወኗቸው ያሉ ሥራዎች በተለይም የሕዝቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ የተሻሉ ቢሆኑም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር የሚተዳደሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በአሁን ጊዜ ለ150 ሺህ ዜጎች ቋሚና ለ89 ሺህ ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሚገኙት የመንግስት የልማት ድርጅቶች በ2015 በጀት ዓመት 924 ቢሊየን ብር ገቢ ማስገባታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሚያስተዳድራቸው ኩባንያዎች አጠቃላይ ኃብት ከ2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱም ተገልጿል።