አገራዊ አንድነትን በማጠናከር የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን ለመመስ ተዘጋጅተናል - ሰልጣኝ አመራሮች

አሶሳ፣ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፡-አገራዊ አንድነትን በማጠናከር የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ መዘጋጀታቸውን በ4ኛ ዙር የመንግስት አመራር ስልጠና የአሶሳ ማዕከል ተሳታፊዎች ገለጹ።

ስልጠናው ዛሬ ሲጠናቀቅ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ታምሩ ኤሊያስ እንዳሉት፣ “ከእዳ ወደ ምንዳ” በሚል የወሰዱት ስልጠና የተሳሳቱ ግንዛቤዎቻችንን ጭምር ያስተካከለ ነው፡፡

"አሁን ህዝባችንን ለማገልገል በላቀ ቁርጠኝነት የተነሳንበት ጊዜ ነው" ያሉት አቶ ታምሩ፣ ለዚህ ደግሞ እንደአመራር ህዝብን አንድ የሚያደርጉ ገዢ ትርክቶች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የህዝቦች አንድነትን ለማጠናከር ከሚያደርጉት በተጨማሪ የልማት ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ወይዘሮ ደመቁ ንጉሴ የተባሉ ሰልጣኝ በበኩላቸው በስልጠናው ጠንካራና ደካማ ጎኖቻችንን ከነመፍትሄዎቻቸው በማስቀመጥ አገርን ማሻገር የሚያስችል አቅም አግኝተናል ብለዋል።

"ወደሥራ ስመለስ በተለይ የሴቶች ተሳትፎን ማሳደግ ዋነኛ ትኩረቴ ይሆናል" ያሉት አመራሯ፣ ለዚህ ደግሞ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በሚገባ በመወጣት በተለይ ለሴቶች አርአያ ለመሆን እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

አገራዊ አንድነት እንዲጠናከር በተለይ አመራር ተግቶ መስራት አለበት ያሉት ወይዘሮ ደመቁ፣ በቀጣይ ወደመጡበት ሲመለሱ ለህዝቦች እብሮነት ትኩረት እንደሚሰጡ ገልጸዋል።  

ወይዘሮ ትሸጋገር ግርማ የተባሉ የስልጠናው ተሳታፊ በበኩላቸው አመራርነት ሃላፊነት ለሰጠን ህዝብ መስዋዕትነት መክፈል ነው ብለዋል። 

ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት አፈጻጸምን ማሳደግ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑንም አክለዋል።

ለእዚህ ደግሞ ራሳቸውን ከብልሹ አሰራር በማራቅ የህዝብ ጥያቄን በአግባቡ ለመመለስ መዘጋጀታቸውን ነው ያስረዱት።

አቶ እንዳልኩህ ሚልኪያ የተባሉ የስልጠናው ተሳታፊም "አገራዊ አንድነትን በማጠናከር የህዝብን ጥቅም የሚጎዱ ጽነፈኛ አስተሳሰቦች እና ድርጊቶችን በመጋፈጥ ሃላፊነቴን እወጣለሁ" ሲሉ ቃል ገብተዋል።

በአሶሳ የስልጠና ማዕከል ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ የመንግስት አመራር ሰልጣኞች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም