በኢትዮጵያ የተጀመረውን የተቋም ግንባታ ሥራ ውጤታማ ለማድረግ አመራሩ ሊተጋ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተጀመረውን የተቋም ግንባታ ሥራ ውጤታማ ለማድረግ አመራሩ ሊተጋ እንደሚገባ ተገለጸ
ጂንካ ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፡- በኢትዮጵያ የተጀመረውን የተቋም ግንባታ ሥራ ውጤታማ ለማድረግ የአመራር አባላት መትጋት እንዳለባቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማዕከል ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ ተናገሩ።
'ከዕዳ ወደ ምንዳ'' በሚል መሪ ሀሳብ ከህዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በጂንካ ማዕከል ሲሰጥ የነበረው 4ኛው ዙር ከፍተኛና መካከለኛ የመንግስት አመራር አባላት የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።
በዚሁ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማዕከል ሚኒስትር ዲኤታና የስልጠና ማዕከሉ አስተባባሪ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ አመራር አባላቱ ከስልጠናው ያገኙት ዕውቀት ለተቋም ግንባታ ማዋል አለባቸው ብለዋል።
የስልጠና ተሳታፊዎች ወቅቱን የዋጀና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ተቋም በማጠናከር ለአገረ መንግስት ግንባታ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
በተለይ አመራሩ ሲተካካ የማይቀያየሩ ጽኑ መሰረት ያላቸውና ዘመን ተሻጋሪ ተቋማት ለመገንባት ትኩረት መስጠት አለባቸው ብለዋል።
ለሀገረ መንግስት ግንባታ ተቋማት ወሳኝ በመሆናቸው በተቋማት ግንባታ ላይ በትኩረትና በጥንቃቄ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስ፣ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተካልኝ ጋሎ በበኩላቸው አመራር አባላቱ ከአቅም ግንባታ ስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደተግባር መቀየር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በተለይም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመዘርጋት የተቋም ግንባታውን ውጤታማ ለማድረግ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጡት አቶ አብዱልፈታህ ኤሊያስ "የአቅም ግንባታ ስልጠናው አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አውዶችን በጥልቀት ለማገናዘብና ልምድ ለመቅሰም ያስቻለ ነው" ብለዋል።
በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም በቀጣይ ጠንካራና ወቅቱን የዋጀ እንዲሁም ጽኑ መሰረት ያለው የተቋም ግንባታ ዕውን ለማድረግና ለህዝቡ ተጠቃሚነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን የመጡት ወይዘሮ ነኢማ አህመድ በበኩላቸው ከስልጠናው ካገኟቸው ዕውቀቶች አንዱ የሪፎርም ሥራዎችን በዘላቂነት ውጤታማ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም በተቋማቸው የተዘረጉ የሪፎርም ሥራዎችን በዕውቀት በመምራት ውጤታማ ለማድረግና ጠንካራ ተቋም ለመገንባት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የለውጥ ሥራዎችን ከግብ ለማድረስ የሚያስችል ጠቃሚ ዕውቀት ማግኘታቸውን የገለጹት ደግም ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን የመጡት አቶ ሸሃባን ሁሴን ናቸው።
ከስልጠናው ባገኙት ዕውቀት መሰረት የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በማዘመን የአርሶና የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በስልጠናው ማብቂያ በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ በስልጠና ማዕከሉ የተሳተፉ የመንግስት አመራር አባላት ከኪሳቸው በማዋጣት በጂንካ ከተማ ለአንድ አቅመ ደካማና ለአንድ አረጋዊ ቤት መስሪያ የሚሆን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ አበርክተዋል።
በድጋፉ ከሦስተኛው ዙር ሰልጣኞች 284 ሺህ 450 ብር፤ ከአራተኛው ዙር ሰልጣኞች ደግሞ 268 ሺህ ብር የተሰበሰበ ሲሆን በገንዘቡም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ቤቶቹ እንደሚገነቡ ተገልጿል።
ከ"ዕዳ ወደ ምንዳ" በሚል መሪ ቃል በተሰጠው የ4ኛ ዙር ስልጠና 701 ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።