የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል አበረታች ስራዎች እንዳከናወነ መመልከቱን ቋሚ ኮሚቴው ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል አበረታች ስራዎች እንዳከናወነ መመልከቱን ቋሚ ኮሚቴው ገለጸ
ሐዋሳ፤ ህዳር 26 / 2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል አበረታች ስራዎች ማከናወን መቻሉን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በክልሉ ባደረገው ምልከታ ማረጋገጡን ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል ያከናወናቸው ሥራዎችን ተመልክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው አባልና የቡድኑ መሪ ወይዘሮ አቡኔ ዓለም እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ በሲዳማ ክልል እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው።
ኮሚሽኑ በሲዳማ ክልል "በተሳታፊ ልየታ፣ በሰው ኃይል ምልመላ፣ በግንዛቤ ፈጠራና የአካታችነት መርሆችን ተከትሎ እየሰራ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል" ብለዋል፡፡
ይህንንም ኮሚሽኑ ካቀረበው ሪፖርት ባሻገር ከማህበረሰቡና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት መገንዘብ መቻላቸውን ጠቁመዋል።
ለአጀንዳ ልየታ የተመረጡ አካላት ማህበረሰቡ በተገቢው መንገድ የመረጣቸውና በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ ያልተነሳባቸው እንደሆኑ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
"ሰነዶችንና በራሪ ወረቀቶችን ማህበረሰቡ በሚረዳው ቋንቋ በማዘጋጀት ሥልጠናና የግንዛቤ መፍጠር ሥራ መሰራቱንም ተመልክተናል" ነው ያሉት።
በሌላ መልኩ አሁንም በተወሰነ መልኩ የግንዛቤ ችግሮች መኖራቸውን አንስተው፤ በቀጣይ የግንዛቤ ማሳደግ ስራው "ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን አስተባባሪና ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ፣ ''የቋሚ ኮሚቴው ምልከታ በጎ የሆኑ ሥራዎችን አጠናክረን እንድንቀጥልና የተስተዋሉ ውስንነቶችን ለማስተካከል ዕድል የሚሰጥ ነው'' ብለዋል።
ኮሚሽኑ በቅድመ ዝግጅትና በዝግጅት ምዕራፉ በሲዳማ ክልል ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች "ከ20 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ሰርቷል" ነው ያሉት።
እንዲሁም አጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ የሚሳተፉ ከ800 በላይ የማህበረሰብ ተወካዮችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመለየት ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡
"ከየወረዳው የተወከሉ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም ከ350 በላይ ለሚሆኑ ተባባሪ አካላት ስለ ምክክሩ አጠቃላይ ሂደትና ዓላማ የግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ተሰርቷል" ብለዋል።
ኮሚሽኑ ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎች ላይ አተኩሮ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ተግባራትን ለማጠናከር በኢትዮጵያ ካሉ መገናኛ ብዙሃን ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ከኮሚሽኑ አመራር አባላት በተጨማሪ ከአስተባባሪ አካላት፣ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከማህበረሰብ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በተለያዩ መድረኮች ተገናኝቶ መወያየቱ ተጠቁሟል።