አየር ኃይል በሰው ኃይል አቅም ግንባታና የትጥቅ አቅምን በማዘመን አመርቂ ሥራዎች አከናውኗል - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
አየር ኃይል በሰው ኃይል አቅም ግንባታና የትጥቅ አቅምን በማዘመን አመርቂ ሥራዎች አከናውኗል - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፡- አየር ኃይል በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የትጥቅ አቅምን በማዘመን፣ በመሠረተ-ልማት ግንባታና በሌሎች ዘርፎች አመርቂ ሥራዎች ማከናወኑን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የአየር ኃይሉን 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል አከባበርን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የማጠቃለያ መርኃ-ግብር ታኅሳስ 6 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድም ገልጸዋል።
የአየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የአየር ምድቦች ሲከበር መቆየቱን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሠረተበትን ኅዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም በመነሻነት ተወስዶ ዘንድሮ 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል እየተከበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ታኅሳስ 6 ቀን 2016 ዓ.ም የበዓሉ የማጠቃለያ መርኃ- ግብር እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
የበዓሉ መከበር ዋና ዓላማ ከለውጡ ወዲህ በአየር ኃይል የተሰሩ ሥራዎችን ለማሳወቅ እንዲሁም ለመጪው ጊዜ የግዳጅ ሥራዎች ለመዘጋጀት ነው ብለዋል።
ከበዓሉ መከበር ግቦች መካከል የተሰሩትን ሥራዎች ማሳወቅና ማስጎብኘት፣ ዕውቅና መስጠትና ሠራዊቱን ማመስገን እንደሚገኙበትም ገልፀዋል።
በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ አመራሮች፣ አብራሪዎች፣ ቴክኒሻኖች እንዲሁም የበረራ አስተማሪዎችና የሌሎችም የምረቃ መርኃ-ግብር ይከናወናል ብለዋል።
አየር ኃይሉ ያስገነባቸው የውጊያ መሠረተ-ልማቶች እንደሚመረቁ ገልጸው፤ የትጥቅ አቅምን ለማሳደግ የተሰሩ ሥራዎች እንደሚጎበኙም ጠቁመዋል።
ምቹ የሥራ አካባቢን ከመፍጠር አንጻር ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው የተለያዩ የውይይት መድረኮች እንደሚዘጋጁም ተናግረዋል።
ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ በአየር ኃይል በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።
በአየር ኃይል ደረጃ ከተቋማዊ ሪፎርም በኋላ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የትጥቅ አቅምን በማዘመንና አዳዲስ ትጥቆችን በመታጠቅ፣ በመሠረተ-ልማትና ምቹ የሥራ አካባቢ ከመፍጠር አንጻር ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዓሉ ሲከበር ከሚከናወኑ መርኃ-ግብሮች መካከልም የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት ጭምር የሚሳተፉበት "ጥቁር አንበሳ" የተሰኘ የአየር ላይ ትርዒት አንዱ ነው ብለዋል።
በሌላ መልኩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የአየር ኃይል አዛዦች የሚሳተፉበት ፎረም እንደሚካሄድ ገልፀው ይህም ወዳጅነትን ለማጠናከር አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡