የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ፍትሃዊ፣ ምክንያታዊና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ፍትሃዊ፣ ምክንያታዊና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ነው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ፍትሃዊ፣ ምክንያታዊና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሐመድ አል አሩሲ አመለከቱ።
ጥያቄውና ፍላጎቱ ሰጥቶ መቀበልን ጨምሮ ሰላማዊ ማዕቀፍና አካሄድን የተከተለ መሆኑን የምክር ቤቱ አባል ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ታሪካዊና የጠለቀ ትስስር እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።
ከ120 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ የባህር በር ጠቀሜታ በቀጥታ የዜጎችን ሕይወት እንደሚነካ ተናግረዋል።
አገሪቷ አሁን ላይ ወደብ ለመጠቀም ከፍተኛ ወጪ እያወጣች መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ የማንንም ጎረቤት አገር ሉዓላዊነት የማይነካና ሰላማዊ አማራጭን የተከተለ መሆኑንም አመልክተዋል።
የባህር በር ጥያቄ ፍትሃዊነትን መሰረት ያደረገና የመጨረሻ ግቡም በጋራ መልማትና መጠቀም መሆኑን ነው የምክር ቤት አባል የሚያነሱት።
የጎረቤት አገራትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎት ከሁሉም አቅጣጫዎች በቅን ልቦና እንዲያዩትም ጠይቀዋል።