ህብረ ብሔራዊ የፌዴራሊዝም ስርዓት በሕዝቦች መካከል አብሮነትና አንድነት እንዲጠናከር አስችሏል-- አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረሃማን - ኢዜአ አማርኛ
ህብረ ብሔራዊ የፌዴራሊዝም ስርዓት በሕዝቦች መካከል አብሮነትና አንድነት እንዲጠናከር አስችሏል-- አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረሃማን
ሐረር፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ):-ህብረ ብሔራዊ የፌዴራሊዝም ስርዓት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አብሮነትና ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር አስችሏል ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረሃማን ገለጹ።
በኦሮሚያ ክልል 18ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በምስራቅ ሀረርጌ ማያ ከተማ ተከብሯል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረሃማን በእለቱ ባደረጉት ንግግር ብሔር ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአብሮነት በከፈሉት መስዋዕትነት የህዝቦች ነጻነትና እኩልነትን ማረጋገጥ ተችሏል።
የዘንድሮውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ስናከብር የጋራ ማንነት፣ አንድነትና አብሮነትን ይበልጥ በማጉላት ነው ብለዋል።
ህብረ ብሔራዊ የፌዴራሊዝም ስርዓቱ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አብሮነትና ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር ማስቻሉንም አፈ ጉባኤዋ ገልጸዋል።
አገሪቱ ለጀመረችው ቀጣይነት ያለው የብልጽግና ጉዞ መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንና ለጎረቤት አገራትም ኢትዮዽያ የለውጥ ምሳሌ እንድትሆን የራሱ ፋይዳ እንዳለውም አመልክተዋል።
ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ትክክለኛና በፅኑ መሰረት ላይ መሆኑን ጠቅሰው በልዩነቶች ውስጥ ውበት፣ አንድነት፣ መከባበርና መፈቃቀርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ህዳር 29 የአገሪቱ ህገ መንግስት የፀደቀበትና የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት የተረጋገጠበት እለት እንዲሁም በቋንቋቸው እንዲማሩ እና ባህልና እሴቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ እድል የሰጠ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አፈ ጉባኤዋ አያይዘውም በዓሉ ሲከበር ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠልና ለተሻለ ድል ለመብቃት ቁርጠኝነት በማሳየት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአስተዳደር ማንነት እና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው፣ በአገሪቱ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተስፋ ሰጪ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የወንድማማችነትና የአብሮነት እሴቶች እየጎለበቱ መምጣታቸውን ገልጸው፣ በሀገራዊ ለውጡ የተገኙ እድሎችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ልዩነቶችን በውይይት በመፍታትና ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሄ በማስቀመጥ ኢትዮጵያን መገንባትና ማበልጸግ ይገባናል ሲሉም አቶ ፍቅሬ አክለዋል።
ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ዘኑባ ኡመር እና ወይዘሮ ሎሚ በቀለ በዓሉ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸውን እንዲያስተዋውቁና የአብሮነት መስተጋብር እንዲያጎለብቱ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እርስ በርስ ያላቸውን አብሮነት እና ትስስር በማጠናከር ለሀገር ሰላም መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል።
"ብዝሃነት እና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በተከበረው በዓል ላይ የፌዴራል፣ የክልሉና የአጎራባች ከፍተኛ ሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።