የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የተሰጥኦ ልማት ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የተሰጥኦ ልማት ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፡- የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሥራ ላይ የሚስተዋሉ የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያደርገውን ጥረት ለማጠናከር ከኢትዮጵያ የተሰጥኦ ልማት ማኅበር ጋር በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ተፈራረመ።
ሥምምነቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሡ ጥላሁንና የኢትዮጵያ የተሰጥኦ ልማት ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር ገመቹ ዋቅቶላ ፈርመውታል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሡ ጥላሁን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በሥራ ላይ የሚስተዋለው የክህሎት ክፍተት ፈታኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ነው።
ይህንንም ችግር ለማቃለል ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው የዛሬው ሥምምነትም የዚሁ አካል መሆኑን ነው የገለጹት።
በሥምምነቱ መሰረት በክህሎት ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተቋማቱ በጋራ ለመሥራት እድል እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የተሰጥኦ ልማት ማኅበር የቦርድ ሊቀ-መንበር ዶክተር ገመቹ ዋቅቶላ በበኩላቸው ማኀበሩ በሥራ እድል ፈጠራና የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት እየሰራ ነው ብለዋል።
ማኅበሩ በሥራ ላይ ያሉ ዜጎች አቅማቸውን የሚያሳድጉበት ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሃሳቦችን ጥናት ላይ ተመስርቶ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።