የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአመራር አባላትን አቅም ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአመራር አባላትን አቅም ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ
ቦንጋ ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የአመራር አባላትን ብቃት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ከፍተኛ የመንግሥት አመራር አባላት ግምገማ መድረክ በቦንጋ መካሄድ ጀመሯል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ የክልሉን አመራር አባላትን አቅም ለመገንባት በየደረጃው ሥልጠናና ግምገማዎች እየተሰጡ ናቸው።
ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህና የልማት ጥያቄዎችን የሚመልሱ ውጤታማ ተግባራት መመዝገባቸውን አስታውቀዋል።
በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር እንደተቻለ የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በግብርናው፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በሌሎች ዘርፎች የተሻሉ አፈጻጸሞች መመዝገቡን ተናግረዋል።
በክልሉ አበረታች የልማት ሥራዎችን ቢከናወኑም፣ በአንዳንድ አመራር አባላት ዘንድ የጋራ ዓላማና ግቦችን የጋራ አድርጎ ከመንቀሳቀስ አኳያ ውስንነት እንደሚታይ ገልጸዋል።
በመሆኑም በግምገማው እነዚህን ነገሮች ጠርተው ወጥና የጋራ የሆነ አገራዊና ክልላዊ አረዳድ በመያዝ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መሥራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
''በየደረጃው ያለውን አመራር በማወያየት፣ በጉዳዮቹ ላይ የጋራ አረዳድ መፍጠርና የመንግሥት ተግባራትን በተገቢው የሚፈፅም አመራር መለየት ይገባናል'' ሲሉም ተናግረዋል።
በክልሉ አንዳንድ የአመራር አባላት የሚስተዋለውን የሥነ ምግባር ግድፈቶችን ፈጥኖ ማረም እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ እንደገለጹት፤ የመንግሥት እሴቶችን፣ ራዕይ እንዲሁም ተልዕኮን በአግባቡ መፈፀምና መተግበር የሚችል አመራር ለመገንባት ሥልጠናዎች ቢሰጡም፤ በአንዳንድ አመራር አባላት ዘንድ የሥነ ምግባር ግድፈቶች ይታያሉ።
በመድረኩ የብሔራዊነት ትርክትን ታሳቢ ያደረገ የአመራር ኃይል አሰላለፍና እሴቶች ላይ የአመራር አባላት አመለካከትና አፈጻጸም እንደሚገመገም አመልክተዋል።
ለአራት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው መድረክ የክልሉ፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች እንዲሁም የከተማ አስተዳደር የአመራር አባላት እየተሳተፉ ነው።