ቀጥታ፡

የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና ትምህርት ማዕከል በአዲስ አበባ ሊመሰረት መሆኑ የኢትዮጵያን ውለታ እውቅና የሚሰጥ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፡-የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና ትምህርት ማዕከል በአዲስ አበባ ሊመሰረት መሆኑ የኢትዮጵያን ውለታ እውቅና የሚሰጥ መሆኑን የማዕከሉ መሥራች እና ቦርድ አባላት ተናገሩ።

የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና ትምህርት ማዕከል ምስረታ ንቅናቄ ተቀማጭነታቸውን እንግሊዝ ባደረጉ በታሪክ፣ ሕግ፣ ባሕል እና ሌሎች ሙያዎች ሰፊ ልምድ ባካበቱ ዝነኛ ጥቁሮች የተመሠረተ ነው።

የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና የትምህርት ማዕከል ጽህፈት ቤቱን በኢትዮጵያ ለመክፈት በመወሰኑ የፊታችን ዓርብ ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ. ም በአዲስ አበባ በይፋ የሚከፈት ይሆናል።

በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለስ የተመራ የዓለም የጥቁር ህዝብ ታሪክ፤ ቅርስ እና ትምህርት ማዕከል መሥራች ቦርድ አባላትን የያዘ ልዑክ አዲስ አበባ ገብቷል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር አብዱ ያሲንን ጨምሮ የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ለልዑኩ አቀባበል አድርገውለታል።

ከአቀባበሉ በኋላ ኢዜአ ያነጋገራቸው የማዕከሉ የቦርድ አባል ሮቢን ዋከር፤ ማዕከሉ ጥቁር ሕዝቦች እስካሁን የጋራ ታሪክ ለማጥናት እና የነገ ዕጣ ፈንታቸው ብሩህ እንዲሆን አይተኬ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።


 

በቅኝ ገዥዎች ተዛብቶ የሚተረክ የጥቁር ሕዝቦችን ትርክት ማስተካከል፣ ዛሬና ትናንትን ሐቀኛ ታሪክ ጥቁሮች ራሳቸው  እንዲጽፉ በማስቻል ለጥቁሮች አንድነትና ትስስር ማጎልበት እንደሚበጅ አንስተዋል።

በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ እና በካሪቢያን ሀገራት የሚኖሩ ጥቁሮችን ታሪክ እና ሀገር በቀል ጥበብ የሚወክሉ ቅርሶች እንዳሉ አስታውሰው፤ በአዲስ አበባ የሚቋቋመውም ተመሳሳይ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ሌላው አባል ጆን ማተው፤ የማዕከሉ መመስረት ከጥንት እስከ ዛሬ ያሉና ያልተነገሩ በርካታ ታሪኮችን፣ ለማውጣት፣ ለመሰነድና ለትውልዱ ለማስተላለፍ የላቀ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።


 

ሌሎች የቦርድ አባላት ሚሼል ሳሙኤል እና ክላሪ ሬድውድ ማዕከሉን በመመስረት የታሪክ አካል በመሆናቸው እንደ ትልቅ ዕድል እንደሚቆጥሩ ገልጸው፤ ማዕከሉ ለመላው ጥቁር ሕዝብ ፈርጀ-ብዙ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።

በተለይም ጥቁር ሕዝቦች የራሳቸውን ታሪክ በራሳቸው ለመተረክ እንዲሁም ቅርሶችን ሰንዶ ለትውልድ ለማሻገር አይተኬ ሚና እንደሚኖረው ነው ያነሱት። 

የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና ትምህርት ማዕከል በኢትዮጵያ እንዲሆን መደረጉ ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የመመረጧ ምስጢርም ምድረ-ቀደምትነቷ፣ የጥቁሮች ቀንዲልነቷ፣ ቅኝ አለመገዛቷ፣ የአፍሪካ ሕብረት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሥራችና ማዕከል በመሆኗ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካዊነት ማበብ፤ ጥቁር ሕዝቦች ከጭቆና ቀንበር እንዲላቀቁ የነበራት ተግባራዊ ድጋፍ እና የአያሌ ቅርሶች ባለቤት መሆኗ ተመራጭ አድርጓታልም ነው ያሉት።

በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁሮችም ተቋሙ የራሳቸው ታሪክ፣ ቅርስና የትምህርት ማዕከል በመሆኑ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ለማዕከሉ ዕውን መሆን ላደረገው ቀና ምላሽና ትብብር መሥራች አባላቱ አመስግነዋል።

የማዕከሉ ዓለም አቀፍ ሊቀመንበር ጸጋዬ ጨማ፤ ማዕከሉን የመመስረት ሃሳብ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ሃሳብ እንቅስቃሴ እንደተጀመረና በ'በቃ' ንቅናቄ እንደ አዲስ እንደተጀመረ ጠቁመዋል።

በመሆኑም ሃሳቡ እውን ሆኖ የፊታችን ዓርብ በአዲስ አበባ በይፋ ጽህፈትቤቱን ከፍቶ ሥራ የሚጀምር ሲሆን፤ በቀጣይም የሙዚየምና ዩኒቨርሲቲ ግንባታዎችን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶችን እየቀረጸ ዕውን ያደርጋል ብለዋል።

የማዕከሉ በአዲስ አበባ መቋቋም ለኢትዮጵያ ትልቅ ዕድል ይዞ የሚመጣ በመሆኑ ሁሉም እንዲደግፈው ጠይቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም