ኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ፣ የባህልና የታሪክ ማዕከል ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ፣ የባህልና የታሪክ ማዕከል ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፡- ኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ፣ የባህልና የታሪክ ማዕከል ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር አብዱ ያሲን ገለጹ።
የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና ትምህርት ማዕከል ዋና ፅህፈት ቤት የፊታችን አርብ ሕዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በይፋ ይመሰረታል።
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ መሪነት የዓለም የጥቁር ህዝብ ታሪክ፣ ቅርስ እና ትምህርት ማዕከል መስራች ቦርድ አባላትን የያዘ ልዑክ አዲስ አበባ ገብቷል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር አብዱ ያሲንን ጨምሮ የሚኒስቴሩ የስራ ኅላፊዎች ለልዑኩ አቀባበል አድርገውለታል።
ማእከሉ በኢትዮጵያ እንዲከፈት መወሰኑ ለኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑን አምባሳደር አብዱ ያሲን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ካላት ገናና ታሪክ እና ለመላው ጥቁር ህዝብ የነበራት አስተዋጽኦ ጋር ተዳምሮ የማዕከሉ በኢትዮጵያ መቋቋም ተጨማሪ የዲፕሎማሲ ስኬት ስለመሆኑም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በማስጠበቅ የዲፕሎማሲ፣ የባህልና የታሪክ ማዕከል እንድትሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አበክሮ መስራቱን ይቀጥላል ብለዋል።
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ፣ ዓለም አቀፍ ጥቁር ህዝብ ታሪክ፣ ቅርስ እና ትምህርት ማዕከል ከሶስት ዓመታት ጥረት በኋላ ከግማሽ ዓመት በፊት የምዝገባው ሂደት ተጠናቆ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱን ገልጸዋል።
ማዕከሉም በአፍሪካ ሕብረት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጋራ ትብብር የፊታችን አርብ በይፋ ተመስርቶ ስራውን እንደሚጀምር ጠቁመዋል።
ማዕከሉ የጥቁር ህዝብ ታሪክን ለመዘከር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በታሪክ ባላት ስፍራ፣ ቀደምት ታሪካዊት ሀገርነቷ እና የአፍሪካ መዲናነቷ ለማዕከሉ መቀመጫነት እንዳስመረጣት ገልጸዋል።
ከትምህርት አኳያ የአፍሪካ ሀገራት የትምህርት ስርዓት እና ፖሊሲ በአፍሪካ በቀል ዕውቀትና እሴቶች እንዲቃኝ የሚያግዝ ይሆናል ብለዋል።
ከቅርስ አኳያም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ቤተ-መዘክር በመገንባት በቅኝ ገዥዎች ተዘርፈው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ቅርሶችን የማስመለስና ጠብቆ ለትውልዶች የማኖር ግብ አለው ተብሏል።
የአፍሪካ ህዝብ ብቻ ሳይሆን መላው ጥቁሮችን ለማሰባሰብ እየተሰራ ባለው ተቋም ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን በማረጋገጥ ሁሉም ድጋፍና እገዛ እንዲያደርግም አምባሳደሮቹ ጠይቀዋል።