የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የማጠቃለያ መርኃ-ግብር ታኅሳስ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የማጠቃለያ መርኃ-ግብር ታኅሳስ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የማጠቃለያ መርኃ-ግብር ታኅሳስ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል ተባለ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የአየር ኃይሉን 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል አከባበርን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የአየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የአየር ምድቦች ሲከበር መቆየቱን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሠረተበትን ኅዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም በመነሻነት ተወስዶ ዘንድሮ 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል እየተከበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ታኅሳስ 6 ቀን 2016 ዓ.ም የበዓሉ የማጠቃለያ መርኃ- ግብር እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
በዓሉ ሲከበር ከሚከናወኑ መርኃ-ግብሮች መካከልም የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት ጭምር የሚሳተፉበት "ጥቁር አንበሳ" የተሰኘ የአየር ላይ ትርዒት አንዱ ነው ብለዋል።
በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ አመራሮች፣ አብራሪዎች፣ ቴክኒሻኖች እንዲሁም የበረራ አስተማሪዎችና የሌሎችም የምረቃ መርኃ-ግብር የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።
አየር ኃይሉ ያስገነባቸው የውጊያ መሠረተ-ልማቶችም የሚመረቁ መሆኑን ጠቁመው፤ የትጥቅ አቅምን ለማሳደግ የተሰሩ ሥራዎች እንደሚጎበኙም ጠቁመዋል።
በሌላ መልኩም የተለያዩ የውይይት መድረኮች የሚዘጋጁ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህም መካከል የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የአየር ኃይል አዛዦች የሚሳተፉበት ፎረም እንደሚካሄድም ገልፀዋል።
የበዓሉ መከበር ዋና ዓላማም በአየር ኃይል ከለውጡ ወዲህ የተሰሩትን ሥራዎች ለሕዝብና ለመንግሥት ለማሳወቅ እንዲሁም ለመጪው ጊዜ የግዳጅ ሥራዎች ለመዘጋጀት ነው ብለዋል።
በበዓሉ መከበር ግቦች መካከልም የተሰሩትን ሥራዎች ማሳወቅና ማስጎብኘት፣ ዕውቅና መስጠትና ሠራዊቱን ማመስገን እንዳሉበት ገልፀዋል።
ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ በአየር ኃይል በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል።
በአየር ኃይል ደረጃ ከተቋማዊ ሪፎርም በኋላ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የትጥቅ አቅምን በማዘመንና አዳዲስ ትጥቆችን በመታጠቅ፣ በመሠረተ-ልማትና ምቹ የሥራ አካባቢን ከመፍጠር አንጻር ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።