የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱ የኃብት ብክነት የሚቀንስና ብልሹ አሠራርን የሚያስቀር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱ የኃብት ብክነት የሚቀንስና ብልሹ አሠራርን የሚያስቀር ነው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፡- የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት የኃብት ብክነት በመቀነስና ብልሹ አሠራርን በመከላከል ቀልጣፋ አገልግሎትን ለመስጠት እንደሚያስችል ተገለጸ።
የግዥ ሥርዓቱ በ2014 ዓ.ም በዘጠኝ የመንግሥት ተቋማት በሙከራ ደረጃ መተግበር መጀመሩ ይታወቃል።
ሥርዓቱ ከዚህ ቀደም በማኑዋል ይፈጸም የነበረውን ግዥ በማስቀረት የመንግሥት ተቋማት የግዥ ፍላጎታቸውን በዲጂታል አሠራር የሚያቀርቡበት አማራጭ ሲሆን፤ ምርትና አገልግሎት አቅራቢዎችን ከገዥዎች ጋር የሚያገናኝ ነው።
ሥርዓቱን እየተጠቀሙ ካሉት ተቋማት መካከል አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ይገኝበታል።
የዩኒቨርሲቲው የግዥ ሥራ አስፈጻሚ አርዓያ ብዙአየሁ፤ ቀደም ሲል የሰነድ ዝግጅት፣ የጨረታ ግምገማና ሌሎች ከግዥ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ከሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው በመሆናቸው ለብልሹ አሠራር የተጋለጡ እንደነበር ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥርዓት (ኢ.ጂ.ፒ.) መግባቱን ገልፀው፤ ይህም በግዥ ሂደቱ ላይ ይነሳ የነበረውን ቅሬታ ያስቀረ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥርዓቱ ምልልስ በማስቀረት ጊዜንና ኃብትን የሚቆጥብ መሆኑን ገልፀዋል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሐጂ ኢብሳ በበኩላቸው፤ አሁን ላይ 163 ተቋማት የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ሥርዓት በመጠቀም ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ሥርዓቱን ወደ ክልሎችና እስከ ወረዳ ባለው የታችኛው እርከን ድረስ እንዲሰፋ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያብራሩት።
ሥርዓቱ ንክኪንና ብልሹ አሠራርን ከማስቀረት ባለፈ ግዥን በዕቅድ እንዲመሩ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት በኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥርዓት ለሚገዙ ንብረቶች 8 ሺህ 700 ጨረታዎች በሥርዓቱ አማካኝነት መውጣታቸውን አመልክተዋል።
በ2015 በጀት ዓመት ከ74 ቢሊየን ብር በላይ የመንግሥት ግዥ በኤሌክትሮኒክ ሥርዓት መፈጸሙን ከመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።