ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ዲጂታል ፕሮቶኮልን ለመተግበር በልዩ ትኩረት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26 / 2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የዲጂታል ፕሮቶኮልን ለመተግበር በልዩ ትኩረት እየሰራች መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ኢትዮጵያ በተሳለጠ የዲጂታል ንግድ ግብይት በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የሚኖራትን ተጠቃሚነት የተመለከተ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

አውደ ጥናቱ የአለም ንግድ ማዕከል ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም አለማቀፍ ተቋማት ተሳትፈውበታል።


 

በመርሐግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር)  ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና መስራች ሀገር እንደመሆኗ ለነጻ ንግድ ቀጠናው ፕሮቶኮል ትግበራ ላይ እየሰራች ነው ብለዋል።

በተለይም የነጻ ንግድ ቀጠናው ልዩ ትኩረት የሰጠውን አህጉራዊ የዲጂታል ንግድ ግብይት ፕሮቶኮል በመተግበር ረገድ በዋነኝነት እየሰራች ትገኛለች ነው ያሉት።

በዚህም በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚያስችል የመሪ ዕቅድ እንዲሁም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ በመንደፍ ተጨባጭ ተግባራትን እየከወነች መሆኑን አውስተዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ መሪ ዕቅድ የነጻ ንግድ ቀጠናውን ለማሳለጥ አይነተኛ ሚና እንዳለው የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው  የዲጂታል ድንበር ዘለል ንግድ ትስስር፣ የቢዝነስ ቁጥጥር ፣ የመረጃ ጥበቃና አዲስ የገበያ ተደራሽነትን የተመለከቱ ፕሮቶኮሎች መካተቱንም ገልጸዋል።

የዘርፉ አጋር አካላት  ለአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ዲጂታል ፕሮቶኮል ትግበራ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።


 

የአለም ንግድ ማዕከል የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ፍቃደ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ 15 ሀገራትን በመለየት የሀገራቱ ምርቶች አለምአቀፋዊ ተደራሽነት እንዲሰፋ እየሰራ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ በመሠረተ ልማት ዝርጋታና ሌሎች ድጋፎች የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ዲጂታል ግብይትን  የሚያግዙ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ነው ሲሉም አመልክተዋል።

በዚህም ወጣቶችና ሴቶችን በዋናነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በአውደ ጥናቱ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እንቅስቃሴን የተመለከቱ ጽሑፎች ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም