በአማራ ክልል የአኩሪ አተር የግብይት ችግርን መንግስት እንዲያቃልል ተጠየቀ 

ባህር ዳር፤ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል የአኩሪ አተር የዋጋ መቀነስን ለማስተካከል መንግስት የገበያ ትስስር እንዲፈጥር   አርሶ አደሮችና   ባለሃብቶች ጠየቁ።

በክልሉ በአኩሪ አተር ሰብል ከለማው መሬት ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ተገልጿል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የኩመር አውላላ ቀበሌ አርሶ አደር ይበልጣል አማረ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በአኩሪ አተር ካለሙት ሦስት ሄክታር መሬት 61 ኩንታል ምርት አግኝተዋል።

ባለፈው ዓመት የአኩሪ አተር ምርት ዋጋ ከተገመተው በላይ በመውረዱ የማምረቻ ወጪያቸውን  መሸፈን ሳይችሉ እንደቀሩም አስታውሰዋል።

"የገበያ ችግር ዘንድሮ ይስተካከላል" በሚል ሰብሉን በስፋት ቢያመርቱም   የገበያ ችግሩ ካለፈው ዓመት የተለየ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ችግሩን ለመቅረፍም መንግስት  የገበያ ትስስር  እንደፈጥርላቸው  አመልክተዋል።

በዚሁ ወረዳ የደለሎ ቀበሌ አርሶ አደር ገብሬ አሻግሬ በበኩላቸው፤ ባለፈው ዓመት በነበረው የገበያ ችግር ተስፋ ሳይቆርጡ በአምስት ሄክታር መሬት ላይ  የአኩሪ አተር ሰብል ማምረታቸውን አስታውሰዋል።

ለአመረቱት ምርት ወጪያቸውን የሚያካክስ "የገበያ ዋጋ ይኖራል" ብለው ተስፋ ቢያደርጉም፤ አሁንም ዋጋው በኩንታል ከ2 ሺህ 500 ብር የማይበልጥ በመሆኑ ለኪሳራ እንዳይዳረጉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። 

አሁን ያለው የገበያ ዋጋ ሰብሉን ለማምረት የወጣውን ወጪ የሚሸፈን እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ የሚመለከተው አካል ሁሉ "ገበያ በማፈላለግ ሊያግዘን ይገባል" ብለዋል። 

ባለፈው ዓመት ያመረቱትን 470 ኩንታል አኩሪ አተር ገበያ ባለመኖሩ እስካሁን በመጋዘን ማስቀመጣቸውን የገለጹት ደግሞ በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ አምሳሉ ላቀው ናቸው።

ዘንድሮም በአኩሪ አተር ካለሙት 20 ሄክታር መሬት 390 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ መንግስት ከኢንዱስትሪዎችና ከላኪዎች ጋር በማስተሳሰር የገበያ ችግራቸውን እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።


 

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ የሚውለው የአኩሪ አተር ምርት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በስፋት እየተመረተ ይገኛል።

ሰብሉ ባለፈው ዓመት በስፋት ቢመረትም ምርቱ የታሰበውን ያህል ዋጋ ማውጣት ባለመቻሉ  አርሶ አደሮችና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች የማምረቻ ወጪያቸውን  መሸፈን ሳይችሉ ቀርተዋል።

ዘንድሮም በ249 ሺህ 728 ሄክታር መሬት ለምቶ እየተሰበሰበ ከሚገኘው የአኩሪ አተር ሰብል ከስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ምርቱ ተገቢውን ዋጋ አውጥቶ በዘርፍ የተሰማሩት ሁሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከአጋር አካላት ጋር ገበያ በማፈላለግ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።


 

በአኩሪ አተር ሰብል የተስተዋለውን የግብይት ችግር ከኢንዱስትሪዎችና ላኪዎች ጋር በማስተሳሰር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የሰብልና የኢንዱስትሪ ምርቶች ግብይት ዳይሬክተር አቶ ልንገረው አበሻ ናቸው።

ከታህሳስ መግቢያ ጀምሮ ለሚጀመረው ግብይትም አቅራቢ ነጋዴዎች፣ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎችና የእርሻ ውል ስምምነት የወሰዱ ባለሃብቶችና ላኪዎች ምርቱን በተገቢ ዋጋ እንዲገዙ ከወዲሁ በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በአኩሪ አተር ከለማው መሬት ከአምስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም