ለህዝቡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ረገድ የሚስተዋሉ የአመራር ግድፈቶች ይታረማሉ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2016(ኢዜአ)፦ህዝቡ በሚፈልገው ልክ ምላሽ ለመስጠት በየደረጃው ባሉ አመራሮች ዘንድ የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት እና በተግባር አፈጻጸም ላይ የሚታየውን ጉድለቶችን በየጊዜው በመገምገምና በማጥራት ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች ክልላዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

ርዕሰ-መስተዳድሩ የግምገማ መድረኩ ወቅታዊ ክልላዊ የፖለቲካ አዝማሚያ በመዳሰስና በመገምገም በየደረጃው በሚያከውናቸው ተግባራት ላይ የፖለቲካ አስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ እንደሆነም ገልጸዋል።

የግምገማና የማጥራት መድረኩም እስከታችው መዋቅር ድረስ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።


 

የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ የብልጽግና ፓርቲ እሴትን፣ ራዕይ እንዲሁም ተልዕኮን በአግባቡ መፈፀምና መተግበር የሚችል አመራር ለመገንባት ክልሉ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

አመራሩ አሁንም የሚታይበትን የአመለካከት ችግር በፍጥነት ማስተካከል እንደሚገባም አመልክተዋል።


 

የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የተሰጡ ቢሆንም አሁንም የሚታዩ ግድፈቶችን አንጥሮ ለማዉጣት ይህ መድረክ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በግምገማ መድረኩ የክልል፣የዞን፣የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን መድረኩ በቀጣይ አራት ቀናት እንደሚቀጥል የደቡብ ምዕራብ ኢትየጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም