በምስራቅ ቦረና ዞን ባለፉት አራት ወራት ከ8 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን ባለፉት አራት ወራት ከ8 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል

ነገሌ ቦረና፤ህዳር 26/2016 (ኢዜአ) ፦ በምስራቅ ቦረና ዞን በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አራት ወራት በ532 ማህበር የተደራጁ ከ8 ሺህ በላይ ወጣቶች ወደ ስራ መግባታቸውን የዞኑ የክህሎትና የስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የስራ እድል ፈጠራ ባለሙያ አቶ ጎዳና ሳራ ዞኑ በተያዘው ዓመት ለ37 ሺህ 619 ስራ ፈላጊዎች የስራ እድል ለማመቻቸት አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በተሰራ ስራም በ532 ማህበር ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ 8 ሺህ 21 ወጣቶች የማምረትና አገልግሎት የመስጠት ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ወደ ስራ ከገቡት ውስጥ 1ሺህ 200 የሚሆኑት የኮሌጂና የዩኒቨርስቲ ምሩቃን ወጣቶች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ወጣቶቹ በግብርና፣ በንግድ፣ በአገልግሎት፣ በማንፋቸሪንግ፣ በግንባታ፣ በማዕድን ፍለጋና ግብይት የስራ ዘርፎች መሰማራታቸውን በማከል፡፡
ወደ ስራው ለተሰማሩት ወጣቶች በከተማና በገጠር አንድ ሺህ 800 ሄክታር መሬትና 27 የማምረቻና የመሸጫ ሼዶች መከፋፈላቸውንም አክለዋል፡፡
የወጣቶቹን ካፒታል ለማሳደግ እንዲረዳም 90 ሚሊዮን ብር የብድር አገልግሎት በሲንቄ ባንክ መመቻቸቱን ባለሙያው አመልክተዋል፡፡
በቅርቡ የስራ እድሉን ተጠቅመው በእንጨትና ብረታ ብረት ስራ ከተሰማሩት ወጣቶች መካከል የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪና የቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርስቲ ተመራቂ ወጣት ከነአን ብርሃኑ አንዱ ነው፡፡
ወጣቱ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ከመስራት ከሶስት ባልደረቦቹ ጋር ተደራጅተው የተሰማሩበት ስራ ከእራሳቸው አልፈው ለሌሎች 13 ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እንዳስቻላቸውም ገልጸዋል፡፡
እሱና ባልደረቦቹ ከሲንቄ ባንክ በወሰዱት 100 ሺህ ብር ብድር የጀመሩት ስራ በአሁኑ ጊዜ ምርታችውን ለአከባቢው ገበያ እያቀረቡ እንደሆነ ገልጿል፡፡
አሁን ባለው የተሻለ የስራ እንቅስቃሴ በቀጣይ እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ብድር በመውሰድ የስራ ዘርፋቸውን ይበልጥ የማስፋት እቅድ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
የቤትና የቢሮ እቃ ምርታቸውን ለተጠቃሚ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን የሚናገረው ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት መሐመድ ሙሳና 14 ባልደረቦቹ ናቸው፡፡
ወጣቱና ባልደረቦቹ ስራ ሲጀምሩ ከመንግስት አንድ የመሸጫ ሼድ እና ከሲንቄ ባንክ ደግሞ የ50 ሺህ ብር ብድር መውሰዳቸውን ገልጿል፡፡