ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለተኪ ምርቶች ትኩረት እንዲሰጡ ልዩ ድጋፍ ይደረጋል-ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም

አዲስ አበባ፤ ህዳር 26/2016(ኢዜአ)፦በሶማሌ ክልል የሚገኙ  አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን ችግር በመቅረፍ ለተኪ ምርት ትኩረት እንዲሰጡ ልዩ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን ገለጹ። 

18ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አስመልክቶ የንግድ ትርዒትና ባዛር በጅግጅጋ ከተማ ትናንት ተከፍቷል። 


 

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን፤ የንግድ ትርኢትና ባዛሩን በከፈቱበት ወቅት የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል አገራዊ አንድነትንና የህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ከፍተኛ አስትዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል። 

የንግድ ትርኢትና ባዛሩ ለአልሚ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ማኅበራት ምርትና አገልግሎታቸውን ለማስተዋወቅ እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ተወዳዳሪነትና ተመጋጋቢነትን በማሳደግ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችል ነው ያብራሩት።

በሆቴል ቱሪዝምና አገልግሎት ሰጪ ዘርፎች ላይ የጅግጅጋ ከተማን ለማነቃቃት ያለው በጎ ተጽዕኖ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በተያዘው በጀት ዓመትም ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን ከ2 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚገመቱ 96 የምርት አይነቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት በትኩረት  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ህብረተሰቡም የአገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህሉን በማሳደግ ተገቢውን ትኩረት ለመስጠት መሰል የንግድ ትርኢትና ባዛር ግብይቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል። 

በሶማሌ ክልል በየደረጃው የሚገኙ አምራቾች የሚያጋጥማቸውን ችግር በመቅረፍ ለተኪ ምርቶች ትኩረት እንዲሰጡ ልዩ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል "ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ እንድነት በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ከትናንት ጀምሮ በመከበር ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም