የሸዋል ኢድ በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገብ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ያጠናክረዋል - -አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26/2016(ኢዜአ)፦ የሸዋል ኢድ በአል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ መመዝገቡ በቱሪዝም ዘርፍ የምናደርገው እንቅስቃሴ እንዲጠናከርና አድማሱን እንዲያሰፋ ያደርገዋል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም ፋራህ የሸዋል ኢድ በዓል በአለም ቅርስነት በመመዝገቡ የእንኳን ደስ ያለን መልዕክት አስተላለፈዋል።

ፓርቲያችን ብልፅግና በትኩረት እና በልህቀት እፈፅማቸዋለው ብሎ ከያዛቸው አምስት የልማት መስኮች መሀል የቱሪዝም ዘርፉ ይገኝበታል ያሉት አቶ አደም በሀገራችን የሚገኙ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ መስህቦችም ይበልጥ እንዲያድጉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሸዋል ኢድ በአል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ መመዝገቡ በቱሪዝም ዘርፍ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በማጠናከር የተሻለ ተጠቃሚነትን እንደሚያሳድግም አስረድተዋል።



ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ሀረር ከተማን በዩኔስኮ ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ የሀገራችን ከተማ የሚያደርጋት ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያንም በርካታ ቅርሶችን በአለም ቅርስነት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራን እንድትይዝ የሚያደርጋት በመሆኑ ደስታችን ወደር የለውም ብለዋል።

በቀጣይም የበአሉ አከባበር ይበልጥ ባማረ መልኩ እንዲቀጥልና ድምቀቱ አለምአቀፍ እውቅናውን በሚመጥን መልኩ እንዲካሄድ፣ ከተማዋም በቱሪስቶች ዘንድ ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን እንደ ብልፅግና ፓርቲ ሰፊ ስራዎችን መስራታችንን እንደምንቀጥል በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እወዳለሁ ማለታቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም