የመተከል ዞን ሠላም መመለስ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በነጻነት ለማከናወን አስችሎናል --ነዋሪዎች 

አሶሳ ፤ኅዳር 26/2016 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ሠላም መመለስ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በነጻነት ለማከናወን እንዳስቻላቸው የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በመተከል ዞን የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ድርቤ ለማ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ባለፉት ዓመታት በአካባቢው ተከስቶ በነበረ የጸጥታ ችግር በተለይ እናቶች እና ሕጻናት ለከፋ ጉዳት ተዳርገዋል።

እሳቸውም በሰላም እጦቱ የሆቴል ሥራቸው ተስተጓጉሎ እንደነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዋ፣ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ሰላም መስፈነን ተከትሎ ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተማሪ ልጆቻቸውን ያለሀሳብ በነጻነት ወደትምህርት ቤት እየላኩ መሆኑንም ነው የገለጹት።

"ከሠላም የሚጠቀመውም ሆነ በሠላም እጦት የሚጎዳው ህብረተሰቡ ነው" የሚሉት ወይዘሮ ድርቤ፣ በአካባቢው አሁን የሰፈነውን ሰላም ዘላቂ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

"የሰላም እጦት የሚያስከትላቸውን ችግሮች ስላየን በቀጣይ ችግሮች ቢከሰቱ እንኳ ተነጋግረን እንፈታለን" ያሉት ነዋሪዋ፣ ከሰላሙ ተጠቃሚ ስለሆንን ከመንግስት ጋር በመሆን ሰላማችንን እንጠብቃለን ብለዋል። 


 

ወጣት ጌታሁን ለገሰ በበኩሉ እንዳለው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በግልገል በለስ ከተማ በክልል ደረጃ መከበሩ የዞኑ ሠላም ዳግም ስለመመለሱ ዋነኛ ማሳያ ነው።

"ከዚህ ቀደም በአካባቢው ተከስቶ ለነበረው የሠላም እጦት ዘረኝነት ዋነኛው ምክንያት ነው" ያለው ወጣቱ፣ ወንድማማችነትና አገራዊ አንድነትን በማጠናከር የተገኘውን ሠላም ለማስቀጠል የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል።

በሰላም እጦት ከግልገል በለስ ወደ ወምበራ፣ ማንኩሽ፣ ፓዌ እና ቻግኒ ከተሞች ተቋርጦ የነበረው የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩን የተናገሩት ደግሞ መምህር ታመነ ሚልኪያስ ናቸው።


 

"አሁን ያለፈውን ረስተን ሥራ ላይ አተኩረን እየተንቀሳቀስን ነው፤ እርስ በርስ ገበያም እየተገበያየን ነው" ሲሉም የሰላምን ትሩፋት ገልጸዋል። 


 

የግልገል በለስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጊሳ ዚፋ በአካባቢው ሰላም በመስፈኑ በከተማው ተቋርጠው የነበሩትን የልማት ሥራዎች ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቱ የአካባቢ ጽዳትና ውበት ሥራን ጨምሮ በጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዘርፎች አደራጅቶ ወደሥራ በማስገባት ከጠባቂነት እንዲላቀቅ መደረጉንም አመልክተዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ እንደ መንገድ፣ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ ያሉ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት አልሚ ባለሃብቶችን  በስፋት ወደ ከተማ በማስገባት የከተማውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ጊሳ አስረድተዋል።

በአካባቢው ለተገኘው ሠላም የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የወጣቶች ማህበራት እና ሌሎች የሠላም አደረጃጀቶች የጎላ ሚና እንደተጫወቱ የገለጹት ከንቲባው፣ እነዚህ አካላት አሁንም ከጸጥታ አስከባሪው ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።


 

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ለሜሳ ዋውያ በበኩላቸው፣ በዞኑ ለመጣው ሠላም ህብረተሰቡና የጸጥታ አካላት ታላቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

በነበረው በጸጥታ ችግር የባከነውን የልማት ጊዜ ለማካካስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በእዚህም የተበላሹ መንገዶችን የመጠገንና የተቋረጠውን ትራንስፖርት አገልግሎት የማስጀመር ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል። 

ለተደራጁ ወጣቶችና ለአርሶ አደሮች የእርሻ ትራክተሮችን ጨምሮ ዘመናዊ የግብርና ቁሶችን ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ለአካባቢው ሰላም መመለስ ቁልፍ ሚና የተጫወቱትን እርቀ ሠላም እና ህዝባዊ የውይይት መድረኮች በአሁኑ ወቅት ተጠናክረው ቀጥለዋል ሲሉም ገልጸዋል።

ዞኑ የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶች እንዳሉት ያመለከቱት ዋና አስተዳዳሪው፣ ይህን ሀብት በአግባቡ በማልማት ለአካባቢውና ለሀገር ጥቅም ለማዋል ህብረተሰቡ ሠላሙን ዘላቂ ማድረግ አለበት ብለዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም