የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮችና ማህበረሰብ አንቂዎች በጠንካራ እሴት በመመራት በአገር ግንባታ ውስጥ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዳማ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ)፡-የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮችና ማህበረሰብ አንቂዎች በጠንካራ እሴት በመመራት በአገር ግንባታ ውስጥ ሚናቸውን እንዲወጡ የሰላም ሚኒስቴር አስገነዘበ።

"የአገር ግንባታ መሰረታዊያን" በሚል ርዕስ ለማህበራዊ ሚዲያ አካላትና ማህበረሰብ አንቂዎች የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንዳኣ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ዜጎች የጋራ ማንነትና ጥቅም ላይ ጥልቅ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከማድረግ አኳያ የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎችና ማህበራዊ አንቂዎች ሚና የጎላ ነው።

"አገር የሚገነባው አንድን መሪ ለማስደሰት ወይም ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ተብሎ አይደለም" ያሉት አቶ ታዬ፤ የብሔር፣ የእምነት፣ የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህልና የሃሳብ ማንነትን የያዘ ብዝሃነት ቢኖረንም "በአገር ግንባታ፣ እና በጋራ እሴቶች ላይ የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ አለብን" ብለዋል።


 

በዚህም የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮችና ማህበረሰብ አንቂዎች አገራዊ ማንነትና ዘላቂ ጥቅምን አውቀው በትክክለኛ እሴት በመመራት በአገር ግንባታ ውስጥ ሚናቸውን እንዲወጡ አቶ ታዬ አስገንዝበዋል።

በተለይም "ህዝቡን በማስተሳሰርና አንድነትን በማጠናከር ላይ መስራት አለባቸው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዚህ ዙሪያ የየማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎችና ማህበረሰብ አንቂዎች የጋራ አረዳድ ሊኖራቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የቅን ልቦና በጎ ስራ ድርጅት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ስንሻው በበኩላቸው፤ ማህበራዊ ሚዲያን እንዴት ለአገር ግንባታና ሰላምን ለማፅናት ማዋል እንችላለን በሚለው ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል።

ማህበራዊ ሚዲያዎችና አንቂዎች "በሃይማኖትና በማንነት ላይ ትኩረት በማድረግ አብሮ የመኖር እሴቶችን በሚሸረሽሩ አጀንዳዎች ላይ ሲሰሩ ይስተዋላል" ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ይኸ ዓይነቱ አካሄድ ለአገር ግንባታ እንደማይጠቅም ተናግረዋል።

በተለይም ቲክቶከሮች፣ ማህበራዊ ገፅና ዩቱበሮች ሰፊ ተከታይ ለማግኘትና ለገቢያቸው በማሰብ ትኩረታቸው በብሔር፣ በፖለቲካ እሳቤ፣ በሃይማኖትና ማንነት መካከል የሚፈጠሩ ክፍተቶችን አጀንዳ በማድረግ ሲሰሩ እንደሚታዩ ገልጸዋል።

"ሁሉም የማህበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎች አንቂዎች ከዚህ እሳቤ በመውጣት በአገርና ሰላም ግንባታ አዎንታዊ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም