በኦሮሚያ ክልል ህጻናትና አቅመ ደካማ እናቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ህጻናትና አቅመ ደካማ እናቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተከናውነዋል

አዳማ ፤ ህዳር 26/2016(ኢዜአ)፦ባለፉት አራት ወራት በኦሮሚያ ክልል ህጻናትና አቅመ ደካማ እናቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት መከናወናቸውን የኦሮሚያ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ገለፀ ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ሰርካለም ሳኩሜ ለኢዜአ አንደገለጹት በተያዘው የበጀት ዓመት በክልሉ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ተከናውነዋል።
በክልሉ በየደረጃው ያሉ የሴቶች ማህበራት፣ የሴቶች ሊግና ፌዴሬሽን የመሳሰሉ የሴቶች አደረጃጀቶች የአካባቢያቸውን ባለሃብቶችና መላውን ህብረተሰብ በማስተባበር አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በተለይም "የእናቶች ቤት ሠርተን እንመረቅ" የሚል መሪ ሐሳብ ተይዞ 62ሺህ 294 የአቅመ ደካሞች ቤቶች እድሳትና ግንባታ ተከናውነዋል ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራው የችግኝ ተከላና እንክብካቤ መርሃ ግብር፣ የደም ልገሳ፣ የጽዳት ስራ፣ የትምህርት ቤቶች እድሳትና ግንባታ፣ ለችግረኛ ተማሪዎች የተደረጉ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ በቢሮው አስተባባሪነት ከተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ብቻ 22 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚገመት የዜግነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መከናወኑን ምክትል ቢሮ ሃላፊዋ ገልጸዋል።
በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ምንም ገቢ የሌላቸው ሴቶች የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸውና ሠርተው ራሳቸውን እንዲችሉ ተደርገዋል ያሉት ደግሞ የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሩቅያ በሹ ናቸው።
22ሺህ 802 የሪቢ በጎችና ፍየሎች እንዲሁም ለጭነት አገልግሎት የሚውሉ ጋሪዎች ተገዝተው ለእናቶች መሰጠታቸው ከተከናወኑት ተግባራት መሆናቸውን በማከል።
በዚህም በተለይም በገጠር ውስጥ በጀርባቸው ተሸክመው ረዥም መንገድ ተጉዘው የሚሰሩ እናቶችን ለመደገፍ የተሰራው ስራ አበረታች መሆኑን በማከል።
በተመሳሳይ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትና በመማር ላይ ለሚገኙ ልጆች የደንብ ልብስን ጨምሮ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በዚሁ መርሃ ግብር መደረጉን ወይዘሮ ሩቅያ ገልጸዋል።
የዜግነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአንድ ወቅት ስራ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት የማህበረሰቡ ባህል ሆኖ እንዲሰራበትም ቢሮው ከክልሉ መንግስት እና ከቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ተገልጿል።