ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ አገራዊ ምክክሩ ጉልህ ሚና አለው - ኮሚሽነር አቶ መላኩ ወልደማሪያም - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ አገራዊ ምክክሩ ጉልህ ሚና አለው - ኮሚሽነር አቶ መላኩ ወልደማሪያም

ሶዶ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሰላም ለማረጋገጥ አገራዊ የምክክር ሂደቱ ጉልህ ሚና እንዳለው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አቶ መላኩ ወልደማርያም ገለጹ።
አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተባባሪ አካላት ስልጠና በወላይታ ሶዶ ከተማ መስጠት ጀመረ።
ስልጠናውን ያስጀመሩት የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መላኩ ወልደማሪያም የአገራችንን ሁለንተናዊ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ምክክሩ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
"አለመግባባቶችና ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ማድረግ እንዲሁም የተፈጠሩትንም በማርገብ የአገሪቷን ሁለንተናዊ ሰላምና ልማት ማረጋገጥ የምክክሩ ዋነኛ አጀንዳ ነው" ብለዋል።
በመሆኑም ይሄ በኮሚሽኑ ስር በሚገኙ 11 ኮሚሽነሮች ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ስልጠናው ተባባሪ አካላትን በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።
ምክክሩ አገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ የተሻለ አማራጭ መሆኑን አመልክተዋል።
ምክክር ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ ብሄርና ሀይማኖት የሚወግን ሳይሆን፤ "የአገርን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለመ ነው" ብለዋል።
በስልጠናው በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 700 ተባባሪ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን፤ ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ ተጠቁሟል።