የብሔር፣ ብሔረሰቦች መኖሪያ የሆነችው ጅግጅጋ እንግዶቿን በደማቅ ሁኔታ እየተቀበለች ነው-ከንቲባ ዚያድ - ኢዜአ አማርኛ
የብሔር፣ ብሔረሰቦች መኖሪያ የሆነችው ጅግጅጋ እንግዶቿን በደማቅ ሁኔታ እየተቀበለች ነው-ከንቲባ ዚያድ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ)፡- ጅግጅጋ ከተማ ለ18ኛው ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዝግጅቷን በማጠናቀቅ እንግዶችን በደማቅ ሁኔታ እየተቀበለች መሆኗን የከተማዋ ከንቲባ ኢንጂነር ዚያድ አብዲ ገለጹ።
ከንቲባው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የጅግጅጋ ነዋሪዎች የበዓሉን ተሳታፊዎች በኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት እየተቀበሉ ነው ብለዋል።
በጅግጅጋ ከተማ 18ኛውን የብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች በዓል በድምቀት ለማክበር ሲደረግ የቆየው የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በበዓሉ ለመታደም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንግዶች ወደ ከተማዋ እየገቡ ነው ያሉት ከንቲባው፥ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የወከሉ የባህል ቡድኖች ጅግጅጋ መግባታቸውን ተናግረዋል።
የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎችም ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቻቸውን በፍቅር ተቀብለው እያስተናገዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የሶማሌ ክልል ህዝብና የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች በዓሉ በድምቀት እንዲከበር በከፍተኛ ጉጉት ሲጠባበቁ ቆይተዋል ብለዋል።
ጅግጅጋ የኅብረ ብሔራዊነት መገለጫና ሰላማዊት ከተማ ናት ያሉት ከንቲባ ዚያድ፥ "የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ተሳታፊዎች፤ እንኳን ወደ ከተማችሁ በሰላም መጣችሁ" ብለዋል።
18ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል "ብዝኅነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ከትናንት ጀምሮ በጅግጅጋ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።