ሰልጣኞች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖችና ለዓፄ ፋሲል ቤተ መንግስት ጥገና የሚውል ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ሰልጣኞች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖችና ለዓፄ ፋሲል ቤተ መንግስት ጥገና የሚውል ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

ባህር ዳር/ጎንደር ፤ ህዳር 25/2016 (ኢዜአ)፡- በባህር ዳርና ጎንደር የስልጠና ማዕከሎች የተሳተፉ የመንግስት አመራር አባላት የአራተኛ ዙር ሰልጣኞች በክልሉ በዝናብ መቆራረጥ በተከሰተ ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እና ለዓፄ ፋሲል ቤተ መንግስት ጥገና የሚውል ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።
“ከዕዳ ወደ ምንዳ”በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳርና ጎንደር የስልጠና ማዕከሎች ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ የአራተኛው ዙር ሰልጣኝ አመራር አባላት የማጠናቀቂያ መርሃግብር ማምሻውን ተካሂዷል።
የገንዘብ ድጋፉ ከሰልጣኝ የአመራር አባላት የተሰበሰበ ሲሆን፤ ይህም እርስ በእርስ በመደጋገፍ ችግሮችን ለመሻገር የተደረገ እንደሆነ ተመላክቷል።
በባህር ዳር ማዕከል የተሳተፉት አመራር አባላት በዝናብ መቆራረጥ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል 527 ሺ ብር ድጋፍ አድርገዋል።
በጎንደር ማዕከል ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩት አመራር አባላት ደግሞ ለዓፄ ፋሲል ቤተ መንግስት ጥገና የሚውል ከ600 ሺህ ብር በላይ በማዋጣት ደግፈዋል።
በባህር ዳር የስልጠና ማዕከል የተገኙት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ ዛዲግ አብረሃ እንደገለጹት፤ ስልጠናው እውቀት ብቻ የተገኘበት ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን ችግሮቻቸውን ለማቃለል መተባበርና መቀናጀት እንዳለባቸው በተግባር ያሳየ ነው።
ሰልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር የኢትዮጵያን ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ መረባረብ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ በአንድ አካባቢ የሚከሰት ችግር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ችግር በመሆኑ ችግሮችን በጋራና በትብብር መፍታት ከአመራሩ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።
በጎንደር የስልጠና ማዕከል ማጠናቀቂያ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ አመራሩ "ኢትዮጵያን በማሻገር ህዝብና መንግስት የጣለበትን ታሪካዊ ሃላፊነት በተግባር በመወጣት የጀመረውን የጋራ ርብርብ መቀጠል አለበት" ብለዋል።
ስልጠናው አመራሩ የተግባር አንድነቱን አጽንቶ በመቀጠል "ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የጎላ ሚና አለው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አመራር አባላቱ በስልጠና ቆይታቸው ያገኙት እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ለህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት የህዝብ ውግንነታቸውን በተግባር ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ በበኩላቸው፤ ሰልጣኞች በጎንደር ቆይታቸው ታሪካዊ ስፍራዎችንና የኢንቨስትመንት ተቋማትን እንዲጎበኙ በማድረግ የልምድ ልውውጥ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡
በስልጠና ማዕከላቱ በማጠናቀቂያ መርሃግብር ላይ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሰልጣኝ አመራር አባላት ተገኝተዋል።