ህብረቱ ባለፈው ዓመት በደቡብ ክልል የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የታዘባቸውን የምርጫ ኩነቶች ይፋ አደረገ

አርባ ምንጭ ፤ ህዳር 25/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ባለፈው ዓመት በደቡብ ክልል የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ የታዘባቸውን የምርጫ ኩነቶች በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።

ህብረቱ በደቡብ ክልል ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ምርጫ የታዘባቸውን የምርጫ ኩነቶች በመገምገም የመጨረሻ ሪፖርቱን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ይፋ አድርጓል።

የህብረቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሃይለማሪያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የህዝበ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከምርጫ አስፈጻሚ አካላት ምልመላ፣ ስልጠናና ስምሪት ጋር በተያያዘ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  ጉልህ ድርሻ እንደነበረው ባደረጉት ትዝብት አረጋግጠዋል።

በሁሉም የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች አምስት አስፈጻሚዎችን መመደቡ ጨምሮ በወላይታ ዞን በተካሄደው ዳግም ምርጫ ስህተቶች እንዳይደገሙ ያበረከተውን አስተዋጽኦ በጥንካሬ አንስተዋል።


 

በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የአገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎች ዴስክ ተጠባባቂ ሃላፊ አቶ ደረጀ ኃይለሚካኤል በበኩላቸው፤ ገለልተኛ የሆኑ አገር በቀል ተቋማት ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሆን ሂደቱን ከመታዘብም በላይ ማህበረሰቡን በማንቃቱ ረገድ የማይተካ ሚና እንደነበራቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት በህዝበ ውሳኔ ሂደቱ የታዘባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ መድረክ አዘጋጅቶ በዚህ መልክ ማቅረቡን አመስግነዋል። 


 

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔው ተዓማኒና በህዝቡ ዘንድ ቅቡልነት ያለው እንዲሆን ገለልተኛ አካላትን በማሳተፍ የወሰደው እርምጃ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ጎበዘ ጎአ ናቸው።

በመድረኩ ላይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካይ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በህዝበ ውሳኔው ሂደት የተሳተፉ ባለድርሻ አካላትና  ሲቪል ማህበራት ተገኝተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም