በመደመር ፍልስፍና ገዥ ትርክቶቻችንን በማጎልበት አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል

ደሴ ፤ ህዳር 25/2016 (ኢዜአ) ፦በኢትዮጵያ "በመደመር ፍልስፍና የሚያሰባስቡን ገዥ ትርክቶቻችንን በማጎልበት አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል" ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የጥናትና ምርምር ክፍል ሃላፊና የኮምቦልቻ ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተተካ በቀለ ገለፁ።

በኮምቦልቻ ከተማ የ4ኛው ዙር የአመራር አባላት ስልጠና የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሄዷል።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የጥናትና ምርምር ክፍል ሃላፊና የወሎ ኮምቦልቻ ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተተካ በቀለ እንደገለፁት፤ በተሳሳተ ትርክት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰሩ ቡድኖችን በጋራ መመከት ይገባል።

የተሳሳተ ትርክት አገርን ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመደመር ፍልስፍና "የሚያሰባስቡንን ገዥ ትርክቶች አጎልብተን አንድነታችንና የእርስ በእርስ ግንኙነታችንን የበለጠ ማጠናከር ይገባናል" ብለዋል።

ለዚህም አመራር አባላት የጠራና የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረው በየደረጃው የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ተለዋዋጭ ሁኔታውን ተገንዝቦ ለህብረተሰቡ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

እንዲሁም ሀብት በማመንጨት ኢኮኖሚውን በማነቃቃት፣ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠርና የፋይናንስ አስተዳደሩን በማዘመን ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚያስችል ግንዛቤ መፈጠሩን ጠቁመዋል።

ሰልጣኞች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና አቅም በመጠቀም ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት በትጋት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የወጣቶች ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ፈዲላ ቢያ በበኩላቸው፤ ስልጠናው አመራሩ የአካባቢውን ፀጋ ለይቶ እንዲያውቅና በአግባቡ መጠቀም እንዲችል እድል መፈጠሩን ገልጸዋል።


 

ከዚህ ባለፈም "የእርስ በእርስ ግንኙነቱን በማሳደግ  ጠንካራና አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት ያግዛል" ብለዋል።

ከሰልጣኞች መካከል አቶ ቃይራኒቶ ገመቹ በበኩላቸው፤ ስልጠናው ጠንካራ አንድነትን በመፍጠር የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ አቅም ፈጥሯል ብለዋል።


 

ያገኙትን እውቀት ተጠቅመውም በመደመር ፍልስፍና የጋራ ትርክቶችን በማጎልበት ለኢትዮጵያ አንድነትና ዘላቂ ሰላም የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

''ስልጠናው የተለያዩ ምልከታዎችና እይታዎች እንዲኖሩን ከማድረጉ ባለፈ አንድነታችንን ለማጠናከር አግዞናል'' ያሉት ደግሞ ሌላዋ ሰልጣኝ አንችንአሉ ዘውዱ ናቸው።


 

''ባህልና እሴቶቻችንን ጠብቀንና የወል ትርክቶቻችንን አጎልብተን የኢትዮጵያ ሁለተናዊ ብልጽግና በጋራ እናረጋግጣለንም'' ብለዋል።

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አመራር አባላትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም