በሚዲያው ዘርፍ የሴቶችን የሙያና የአመራርነት ተሳትፎ ለማሳደግ የሚዲያ ተቋማት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በሚዲያው ዘርፍ የሴቶችን የሙያና የአመራርነት ተሳትፎ ለማሳደግ የሚዲያ ተቋማት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 25/2016 (ኢዜአ)፡- በሚዲያው ዘርፍ የሴቶችን የሙያና የአመራርነት ተሳትፎ ለማሳደግ የሚዲያ ተቋማት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፤ በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ በተመለከተ ከባለሥልጣኑና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፤ በሚዲያው ዘርፍ የሴቶች የሙያና የአመራርነት ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
የሚዲያ ኢንዱስትሪ የሴቶች ተሳትፎ ካልታከለበት የሚፈለገው እድገት የማይሳካ በመሆኑ ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውን ለማጠናከር የሁላችንም እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለይም የሚዲያ ተቋማት የሴቶችን የሙያና የአመራርነት ተሳትፎ ለማሳደግ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበር የቦርድ አባል መሠረት ከበደ፤ ማኅበሩ በ2015 ዓ.ም ሴቶች በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ በተመለከተ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ጥናት ማድረጉን ገልፀዋል።
በጥናቱም በሀገሪቱ የሚገኙ አብዛኛዎቹ የመገናኛ ብዙኃን የሥርዓተ-ፆታ ፖሊሲ እንደሌላቸው ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።