ወጣቶች ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ተግተው እንዲሰሩ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ተግተው እንዲሰሩ ተጠየቀ

ደብረ ብርሀን፤ ህዳር 25 /2016 (ኢዜአ)፦ ወጣቶች ለምክንያታዊና ማህበረሰባዊ እሴቶች ተገዥ በመሆን ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ተግተው በመስራት የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
“ብዝሀነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት“ በሚል መሪ ሃሳብ 18ኛውን የብሔሮች ፣የብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ዛሬ በደብረ ብርሀን ከተማ ተከብሯል።
የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ መንግስቱ ቤተ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ እየተመዘገቡ ላሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች የወጣቶች ድርሻ የጎላ ነው።
በዓሉን ስናከብር በማህበረሰቡ ውስጥ ለዘመናት የቆዩ የአንድነት፣ የእኩልነትና የሰላም እሴቶች ግንባታ በማዳበር እኩልነትና ብዝሀነትን እንዲጎለብት ለማድረግ ነው ብለዋል።
ወጣቶች ከስሜታዊነት ወጥተው ምክንያታዊነት በማስቀደም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ተግተው በመስራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተክለየስ በለጠ በበኩላቸው፤ ሰላም፣ ፍትህና ልማትን ለማጠናከር ወጣቶች አንድነትን አጎልብተው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ወጣቶች ከማህበራዊ እሴት ተፃራሪ ከሆነ ነገር ራሳቸውን በማራቅ ለኢትዮጵያ ሰላም በጋራ መስራት እንደሚገባቸው የተናገሩት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ወጣትና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ምትኩ ማሙሻ ናቸው።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወጣት ብዙ አየሁ ጌታቸር በሰጠው አስተያየት፤ የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት የፀደቀበትን እለት ስናከብር አንድነትን፣ ሰላምን፣ ተከባብሮና ተሳስቦ የመኖር ጥበብን በማሰብ መሆን አለበት ብሏል።
ለበዓሉ በተዘጋጀው መድረክ የሰላም ግንባታ ጽንሰ ሀሳብ፣ ሰላም በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን እይታ የሚሉ ጽሁፎች ቀረበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።