ቀጥታ፡

በአፋር ክልል ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የሚያሰባስቡ ተወካዮች ምርጫ እንደቀጠለ ነው

ሰመራ ፤ ህዳር 25/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል 48 ወረዳዎችና ከተማ መስተዳድሮች ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የሚያሰባስቡ ተወካዮች ምርጫ መቀጠሉን አስታወቀ።

የተወካዮቹ ምርጫ ትናንት በዱብቲ ወረዳ፣ በዱብቲ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በጭፍራ ወረዳ የተከናወነ ሲሆን ዛሬ ደግሞ በአይሳኢታና በአደአር ወረዳዎች ተካሂዷል።

ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ እንዲያሰባስቡ የሚመረጡት የጎሳ መሪዎች፣ የሐገር ሽማግሌዎች፣ አርብቶ አደሮች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ የንግድ ማህበረሰቡና ተፈናቃዮች ናቸው።

ለዚህም ከእያንዳንዱ ወረዳ ወይም ከተማ አስተዳደር 18 ተወካዮች የተመረጡ ሲሆን፣ በምርጫ ሂደቱም እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል በሁለት ሰዎች ይወከላል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሸነር ዶክተር አይሮሪት መሐመድ እንዳስረዱት ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምክክር የሚሆን አጀንዳ ለማሰባሰብ የተለያዩ ማህበረሰቦችን የሚወክሉ ተሳታፊዎችን መሥፈርት ባደረገ መልኩ እያስመረጠ ነው።


 

የመረጣ ሂደቱም ተወካዮቹ የተወከሉበትን ማህበረሰብ ክፍል ድምፅ የሚያሰሙ፣ መልካም ስብዕና የተላበሱ፣ ተዓማኒነትና ተቀባይነት እንዳላቸው ባረጋገጠ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል።

መስፈርቱ ተመራጮቹ የሚወክሉት ማህበረሰብ በሚያነሳቸው ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ መያዛቸውን እንደሚያካትት ዶክተር አይሮሪት አመልክተዋል።

የተወካዮቹን ምርጫ የሚያስተባብሩት አቶ አሊ ጀማል በሰጡት አስተያየት ኮሚሽኑ ያዘጋጀው መድረክ በቀጣይ በሀገር ደረጃ ለሚካሄደው ምክክር የማህበረሰቡን ተወካዮች በቀጥታ መምረጥ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በየአካባቢው እየተካሄደ ያለው ምርጫ ተወካዮቹ የወከላቸውን ማህበረሰብ ጉዳዮች በዝርዝር በማቅረብ ሚናቸውን ለመወጣት እንደሚያስችላቸው አቶ አሊ ገልጸዋል።

ከዱብቲ ወረዳ የተወከለው ወጣት መሐመድ ጁሃር በበኩሉ የወረዳው ወጣቶችን ፍላጎትና የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ የሚሰሩ ተወካዮችን መምረጡን ተናግሯል።

የተወካዮቹ ምርጫ ነገ በአፋምቦ፣ በኮሪ ሚሌ እና በኤሊዳአር ወረዳዎች በሚካሄድ ምርጫ እንደሚጠናቀቅ ኮሚሽኑ ያዘጋጀው መርሐ ግብር ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም