ቀጥታ፡

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ በጅግጅጋ የንግድ ትርዒትና ባዛር ተከፈተ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 25/2016(ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ በጅግጅጋ ከተማ የንግድ ትርዒትና ባዛር ተከፈተ።

18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ ሁነቶች ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚከበር ይሆናል።

ሕዳር-25 "የወንድማማችነት" ቀን ተብሎ እየተከናወነ ባለው መርሃ-ግብር በጅግጅጋ ከተማ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር የተካሄደ ሲሆን፤ በመቀጠልም የንግድ ትርዒትና ባዛር ተከፍቷል።


 

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን፤ የንግድ ትርዒትና ባዛሩን በይፋ መርቀው ከፍተዋል። 

በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አመራርና አባላት፣ የሶማሌ ክልል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ታዳሚዎችም ተገኝተዋል። 

በጅግጅጋ ከተማ እየተከበረ ያለው 18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል። 

በመቀጠልም ኅዳር-26 የብዝኃነት፣ ኅዳር-27 የአብሮነት፣ ኅዳር-28 የመደመር፣ እንዲሁም ኅዳር-29 የኢትዮጵያ ቀን በሚሉት ስያሜዎች መከበሩ የሚቀጥል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም