በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ለልማት የሰጡትን ትኩረት ለሙስና መከላከሉም እንዲሰጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ለልማት የሰጡትን ትኩረት ለሙስና መከላከሉም እንዲሰጡ ተጠየቀ
አሶሳ ፤ ህዳር 25/2016(ኢዜአ) ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ለልማት የሰጡትን ትኩረት ለሙስና መከላከሉ ሂደትም እንዲሰጡ የክልሉ ስነ-ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ጠየቀ፡፡
የክልሉ ስነ-ምግባር እና ጸረሙና ኮሚሽን በሙስና መከላከል ላይ ያዘጋጀው ውይይት ዛሬ በአሶሳ ተካሄዷል፡፡
ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ በወቅቱ እንዳሉት ኮሚሽኑን ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ለመስራት አደረጃጀቱን አጠናክሯል፡፡
''በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት 165 ሺህ ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አግኝተዋል'' ያሉት ኮሚሽነሩ በክልሉ 33 ሺህ 856 ሰዎች ሃብታቸውን አስመዝገበዋል ብለዋል፡፡
በነዚሁ ዓመታት ክልሉ 919 የሙስና ጥቆማዎች እና አቤቱታዎችን ተቀብሎ ምርመራ በማድረግ 65 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የህዝብ እና የመንግስት ሃብት ከምዝበራ ለማዳን ተችሏል ነው ያሉት፡፡
እንዲሁም ያለአግባብ በግለሰቦች የተወሰደ 99 ሺህ ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ እንዲታገድ ማድረጉን ኮሚሽነሩ አመልክተዋል፡፡
የሃብት ምዝገባን ተከትሎ ሰባት መኖሪያ ቤቶች እና አራት የንግድ ድርጅቶች በፍርድ ቤት መታገዳቸውን አስረድተዋል፡፡
አመራሩ፣ ማህበረሰቡ እና ባድርሻ አካላት ለልማት የሰጡትን ትኩረት በሙስና መከላከሉ እንዲያጠናክም ኮሚሽር መንግስቱ ጠይቀዋል፡፡
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሂ በበኩላቸው በክልሉ በ2014 በጀት ዓመት ብቻ በመንግስት ተቋማት ከ59 ሚሊዮን ብር በላይ የኦዲት ግኝት መቅረቡን አመልክተዋል፡፡
የኦዲት ግኝቱን ከማስመለስ ባለፈ የህግ ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ እንደሚሰራ ገልጸው በተለይም ለሙስና ዋነኛ ምንጭ ከሆኑት መካከል የጨረታ ሂደትን ለማስተካከል ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ በበኩላቸው በመንገድ ዘርፍ ህገወጥ መንጃ ፈቃድ፤ በትራንስፖርት ዘርፍ ደግሞ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እና ሌሎችም ዋና የሙስና ምንጮች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
ችግሩ የሚታይባቸውን ዘርፎች ኮሚቴ አቋቁሞ ክትትል እያደረገ ከመሆኑም በተጨማሪ በቴክኖሎጂ በማደራጀት ህገወጥነትን ለማቆም የጀመረው ጥረት እንደሚያጠናክር ተናግረዋል፡፡
''ሙስና በትምህርት ዘርፍም ፈተና ነው'' የሚሉት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አወቀ አይሸሽም ናቸው፡፡
ቢሮው ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በአፍ መፍቻ ቋንቋዎች የስነ-ምግባር ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው በ51 ትምህርት ቤቶች የተከፈቱ ክበባትም መረጃ በመስጠት የድርሻቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል፡፡
''ሙስናን መከላከል ከራስ ይጀምራል'' ያሉት ደግሞ በክልሉ ምክር ቤት የፍትህ፣ ሠላም እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጌታነህ ሰዲ ናቸው፡፡
በክልሉ ሃብትን በማስመዘገብ እና ሌሎችም ሙስናን በመከላከል የሚታዩ ጉዳዮች የሚበረታቱ ቢሆንም በየጊዜው ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የሚቀሩ የልማት ፕሮጀክቶች ለሙስና በር የሚከፍቱ በመሆኑ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ ተገቢውን ክትትል እንደሚዲረግ ጠቁመው በተለይ ሙስናን ለመከላል በሚደረገው ሂደት ተቋማት ተቀናጅተው ቢሰሩ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡