ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ ተወካዮች በፍትሃዊነት  እንዲሳተፉ እየተመቻቸ ነው 

ሶዶ፤ ህዳር 25 / 2016 (ኢዜአ)፡- በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ ተወካዮች በፍትሃዊነት እንዲሳተፉ የማመቻቸት ስራ እየተካሄደ መሆኑን  የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀገራዊ ምክክሩ ተባባሪ አካላት ስልጠናን ለመስጠት  ዝግጅት ማጠናቀቁን አስመልክቶ ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ መግለጫ ሰጥቷል። 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በመግለጫው እንዳመለከቱት፤ ኮሚሽኑ ከሚያከናውናቸው  ተግባራት ውስጥ የምክክር ተሳታፊዎችን መለየት ዋነኛው ነው።

ለዚህም በተለያዩ ክልሎች ሲሰራ መቆየቱን አውስተው፤  በአሁኑ ወቅትም ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክክሩ ተሳታፊ የሚሆኑ አካላትን  ለሚለዩ ተባባሪ አካላት ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

የስልጠናው ዓላማ ተባባሪ አካላቱ በምክክሩ የሚሳተፉ አካላትን ገለልተኝነትና አካታችነት በማረጋገጥ በጥንቃቄ እንዲመርጡ ለማስቻል መሆኑን ዶክተር ዮናስ ተናግረዋል። 

እንዲሁም የስራውን ሂደትና በአጠቃላይ የምክክሩ ፅንሰ ሃሳብ ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር ሰላምን መገንባትና ምክክርን ባህል ማድረግ የኮሚሽኑ ዋንኛ አጀንዳዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ኮሚሽኑ 30 በመቶ ሴቶችና ወጣቶችን እንዲሁም ስድስት በመቶ አካል ጉዳተኞችን እንደሚያሳትፍም ጠቅሰዋል። 


 

አክለውም የኮሚሽኑ ስራ ቀጣይነት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለያዩ የልማት፣ የብልጽግናና የሰላም ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ለምክክር ሂደቱ መሳካት መላው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርቧል። 

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ መላኩ ወልደማሪያም በበኩላቸው፤ ምክክሩ  ሀገርን እንደ አዲስ የመገንባት ጉዳይ በመሆኑ መዘግየት ቢስተዋልም እኩልነትና ነፃነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር  ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል። 

 የህዝብ ችግሮችን በብቃት ለመፍታት ሰላም ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ያመላከቱት ኮሚሽነሩ ፤ ሰላምን  ለማረጋገጥ ተስፋ ሰጪ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል። 

ስልጠናውን የሚወስዱ ተባባሪ አካላት በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን፣ የሀይማኖት ተቋማትን፣ ሲቪክ ማህበራት ምክር ቤትን ጨምሮ ሌሎችንም  የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ ተሳታፊዎችን  እንደሚለዩ አብራርተዋል።  

ከህዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣዮቹ ሶስት ቀናት በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚካሄደው ስልጠና ላይ ከሁሉም የክልሉ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 700 ተባባሪ አካላት እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም