የቱሪዝም መዳረሻዎች የሀገሪቱ የሀብት መፍጠሪያ አማራጭ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው-ቱሪዝም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝም መዳረሻዎች የሀገሪቱ የሀብት መፍጠሪያ አማራጭ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው-ቱሪዝም ሚኒስቴር
ሮቤ ፤ ህዳር 25/2016(ኢዜአ) ፦ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሀገሪቱ የሀብት መፍጠሪያ አማራጭ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።
የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የባህልና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) በቅርስነት መመዝገቡን በማስመልከት የማስተዋወቅ ስራ በባሌ ሮቤ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተካሄዷል።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚንስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንዳሉት የቱሪዝም መዳረሻዎች የሀገሪቱ የሀብት መፍጠሪያ አማራጭ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው።
የተፈጥሮ ኃብትን በመንከባከብና በመጠበቅ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ በማድረጋቸው የባሌ ህዝብ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
ከረዥም ጊዜ ቆይታና ውጣ ውረድ በኋላ የባሌ ተራሮች የዓለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ሰነድ በማዘጋጀት፣ የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራትና እስከ ህይወት ማስዋዕትነት ለከፈሉ አካላት ምስጋና እንደሚገባቸውም ሚኒስትሯ አክለዋል።
ቅርሱ በዩኔስኮ በቋሚነት መመዝገቡ ለቱሪዝም እድገት ለማዋል የሚያግዝ መሆኑንና ፓርኩን አልምቶ ይበልጥ ተመራጭ የቱሪዝም ስፍራ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
መንግስት ቱሪዝም የኢኮኖሚ ምሰሶና የብልፅግና መሰረት እንዲሆን ግብ ጥሎ እየሰራ እንደሆነም ነው ያስታወሱት።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር በግል የጻፉት የመደመር መፅሃፍ ከሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ለቱሪዝም ልማት እንዲውል ማበርከታቸውን አስታውሰዋል።
ሚኒስቴሩም የቱሪዝም መዳረሻዎች የሀገሪቱ የሀብት መፍጠሪያ አማራጭ እንዲሆኑ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በምክትል ፕሬዝዳንት መዕረግ የኦሮሚያ ክልል የግብርና ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱረህማን አብደላ በበኩላቸው፣ የክልሉን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ ከኢንዱስትሪና ግብርና ባልተናነሰ የቱሪዝም ልማት ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
በተለይም በክልሉ የሚገኙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦችን ይበልጥ በማልማት የቱሪስት ፍሰትን የሚጨምሩና ቆይታን የሚያራዝሙ ሥራዎች ትኩረት አግኝተዋል ነው ያሉት።
በተለይም የቱሪዝም ዘርፉን ብቻ የሚከታተል ራሱን የቻለ የቱሪዝም ኮሚሽን መቋቋሙ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ አብዱረህማን አክለውም የክልሉ መንግስት የቱሪዝም ልማቱ ለክልሉ ብሎም ለአገር ኢኮኖሚ እንዲውል 18 አዳዲስ የኤኮቱሪዝምና 24 ፓርኮች ተለይተው እንዲደራጁ መደረጉን ለአብነት አንስተዋል።
የባሌ ተራሮች ይዘቱን ጠብቆ ለዓለም ቅርስነት እንዲውል በማድረጉ በኩል የባሌ ህዝብ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ናቸው።
ፓርኩን በዓለም ቅርስነት ማስመዝገቡ ብቻውን ግብ አይደለም ያሉት አቶ ኩመራ፤ ህዝቡ የፓርኩን ጥበቃ ይበልጥ በማጠናከር በዩኔስኮ መዝገብ ላይ በማቆየት የቆየ ባህሉን ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
ፓርኩን በመንከባከብና በመጠበቅ ለዓለም ቅርስነት ላበቃው የባሌ ህዝብ ክብር ይገባዋል ያሉት የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ ናቸው።
የብዙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦች ባለቤት የሆነው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ይበልጥ በማልማት ለአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ ለአገር ኢኮኖሚ እንዲውል ዞኑ ጠንክሮ ይሰራል ነው ያሉት።
በፕሮግራሙ ላይ ፓርኩን በዩኔስኮ በቋሚነት በማስመዝገብ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ለነበራቸው ባለድርሻ አካላት የዕውቅና የምስክር ወረቀትና የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።
ፓርኩ ዋቤ ሸበሌ፣ ዱማል፣ ያዶትና ወልመል የተሰኙ ወንዞች የሚፈሱበትና ቀይ ቀበሮ፣ የደጋ አጋዘንና ሌሎችም ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ አዕዋፋትና ዕጽዋት መገኛ መሆኑ ይታወቃል።