የሸገር ከተማ አስተዳደር ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሸገር ከተማ አስተዳደር ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገለጸ
ክልል፤ ህዳር 25/2016(ኢዜአ) ፡- የሸገር ከተማ አስተዳደር ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ጉዮ ገልገሎ ገለጹ።
ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በአገሪቷ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ የተለያዩ ተጽእኖዎችን እያደረሰ ይገኛል።
ለአብነት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ሶስት ወራት በ402 የንግድ ድርጅቶች ላይ በተደረገ የክትትልና የቁጥጥር ስራ ህግን ተከትለው ባልሰሩ 37 ንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን መግለጹ ይታወቃል።
እርምጃው የተወሰደባቸውም የንግድ ድርጅቶቹ ከተሰጣቸው የንግድ ፈቃድ መስኮችና ዓላማዎች ውጪ ሲሰሩ የነበሩ፣ ባልፀና ወይም ባልታደሰ ንግድ ፊቃድ ሲነግዱ የተገኙ፣ ባስመዘገቡት የስራ አድራሻ ያልተገኙ እንዲሁም የቅርንጫፍ አድራሻ ያላስመዘገቡ በመሆናቸው እንደሆነ በማከል ።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በየሳምንቱ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ከፍተኛ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ከአገር ሲወጡና ሊገቡ ሲሉ እየተያዙ መሆኑን ያመለክታል።
ኮሚሽኑ ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 5 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 284 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የገቢ እና የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዙን በድረ ገጹ ማስፈሩምይታወሳል።
ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በአገሪቷ ካሉ ዋና ዋና ከተሞች መካከል በቅርቡ የተመሰረተው የሸገር ከተማ አስተዳደር ምን ዓይነት ተሞክሮ እንዳለው ተጠይቋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሸገር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጉዮ ገልገሎ፣ ከተማ አስተዳደሩ ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ መከላከል ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ አስተዳደሩ ባደረገው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ከህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ 58 ሚለዮን ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።
ፉሪ፣ ሰበታ፣ ቡራዩና ጣፎ አካባቢዎች ደግሞ የኮንትርባንድ ንግዱ በብዛት የሚተላለፍባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተጠቀሱት ስፍራዎች ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት በሩብ ዓመት ብቻ 28 ሚሊዮን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ገልጸዋል።
በቀጣይም የቁጥጥር ስራው እንደሚጠናከር ገልጸው አስተዳደሩ በድርጊቱ ተሳትፈው የተገኙ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰዱን ይቀጥላል ብለዋል።
የሸገር ከተማ አስተዳደር በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎችን ይዞ የተመሰረተ ከተማ መሆኑ ይታወሳል።