በጋምቤላ ክልል የስራ እድል አማራጮችን በማስፋት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የስራ እድል አማራጮችን በማስፋት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ነው
ጋምቤላ ፤ ህዳር 25 /2016 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል የስራ እድል አማራጮችን በማስፋት የዜጎችን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
የክልሉ የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት ጉባኤ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ጉባኤውን የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት ፤ በክልሉ ባለው ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት የስራ እድል አማራጮችን በማስፋት የስራ አጥ ዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል።
በክልሉ ለስራ አጥ ወጣቶች የሚውል ሰፊ የውሃ ፣የመሬት፣ የማዕድንና የቱሪዝም ሀብት መኖሩን ጠቁመው፤ ያለ ስራ የተቀመጠውን ወጣት ኃይል በማሰማራት በፍጆታ ምርቶች እራስን መቻል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማፋጠን ክህሎት መር ፈጠራን ማሳደግና ወጣቱን ከስራ ጠባቂነት አስተሳሰብ ወደ ስራ ፈጣሪነት መቀየር እንዳለበትም አመልክተዋል።
የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰናይ አኩዎር በበኩላቸው፤ ቢሮው የስራ አጥነት ችግሮችን ለመቀነስ የሚያስችል ዕቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የስራ ዕድል ለሚፈጠርላቸው ዜጎችም 106 ሄክታር የገጠርና የከተማ መሬት ለመስሪያና ለመሸጫ ለማዘጋጀትም እየተሰራ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል።
አዳዲስ የስራ ፈጠራ ሃሳቦችን በማበረታታትና በማስፋት ተወዳዳሪና ውጤታማ የሆኑ ወጣቶችን ለማፍራትም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።