ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በጅግጅጋ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 25/2016 (ኢዜአ) ፡-18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በጅግጅጋ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው።

በዛሬው እለት የወንድማማችነት ቀን በሚል የተጀመረው ክብረ በዓል እስከ ቅዳሜ በተለያዩ ስያሜዎች የሚቀጥል ይሆናል። 

ሕዳር 25 የወንድማማችነት ቀን ተብሎ እየተከናወነ ባለው መርሃ ግብር የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሂዷል።


 

በውድድሩም በወንዶች አትሌት አህመድ መሀመድ እንዲሁም በሴቶች አትሌት ቃል-ኪዳን አይችሌ አሸናፊ ሆነዋል። 

ከጅግጅጋ አትሌቲክስ ፕሮጀክት የተገኙት አትሌት አህመድ መሀመድ፣ አትሌት በረከት መሀመድ እና አትሌት መሀመድ አህመድ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል። 


 

በሴቶች ደግሞ ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ አትሌት ቃል-ኪዳን አይችሌ፤ ከጅግጅጋ አትሌቲክስ ፕሮጀክት አትሌት ዝናሽ ትዕግስቱ፤  አትሌት በሻቱ ተካ ደግሞ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል። 

በዝግጅቱ ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የሶማሌ ክልል መንግስት እና የጅግጅጋ ከተማ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ከሕዳር 25 እስከ ሕዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት እና በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት "ብዝኅነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሐሳብ በጅግጅጋ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው። 

በዚህም ሕዳር-25 የወንድማማችነት፣ ሕዳር-26 የብዝኃነት፣ ሕዳር-27 የአብሮነት፣ ሕዳር-28 የመደመር፣ ሕዳር-29 የኢትዮጵያ ቀን በሚሉ መሪ ስያሜዎች በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ጀምሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም