የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ለብሔራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነት መጠናከር ትልቅ ፋይዳ አለው- የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ለብሔራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነት መጠናከር ትልቅ ፋይዳ አለው- የምክር ቤት አባላት
አርባ ምንጭ ፤ ህዳር 25/2016 (ኢዜአ) ፡- የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በየዓመቱ መከበሩ የህዝቡን ዕሴቶች በማስተዋወቅ ብሄራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የጋሞ ዞን ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
ኢዜአ ከብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ጋር በተያያዘ ያነጋገራቸው የጋሞ ዞን ምክር ቤት አባላት እንዳሉት፤ የበዓሉ መከበር ለብሔር-ብሔረሰቦች እሴቶች መተዋወቅና አብሮነታቸውን ለማሳየት እንዲሁም ለብሄራዊ መግባባትና ለአገራዊ አንድነት መጠናከር ፋይዳው የላቀ ነው፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የጋሞ ዞን ህዝብ ምክር ቤት የሴቶችና ወጣቶች ማህራበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ዳርዛ ብዝሃነትን በማስተናገድ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲመጣ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔር ብሔረሰቦች መብት በህገ-መንግስቱ ዕውቅናና ዋስትና ማግኘቱ ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በማድረግ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልማት ላይ ቀጥታ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውብ ባህል፣ እሴትና የተፈጥሮ ፀጋ አላት ያሉት አቶ ዳንኤል እነዚህን ለማጉላትና ለመጠቀም ብሎም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መጎልበትም በዓሉ የጎላ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
ብሔር ብሔረሰቦች ግጭትን ሊያነሳሱ የሚችሉ ችግሮችን በጋራ በመፍታት በሀገራችን የሰላም ግንባታ ሂደት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ተዋዶ፣ ተከባብሮና ተቻችሎ ከመኖር ውጪ አማራጭ የለውም ያሉት አስተያየት ሰጪው ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በማጎልበት የወል እውነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ህዝቡ ባህልና እሴቱን እንዲያስተዋውቅ፣ ልምድ እንዲለዋወጥ፣ እርስ በርስ እንዲተዋወቅና ግንኙነቱን እንዲያጠናክር የሚግዝ ነው ያሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ጥሩነሽ ተስፋዬ ናቸው፡፡
የብሔር ብሔረሰቦች የመመረጥም ሆነ የመምረጥ፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ ሀብት የማፍራትና የመኖር መብት በህገ-መንግስቱ የተረጋገጠ በመሆኑ በልምምድ በማሳደግና በማጎልበት በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡
የዘንድሮው 18ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን “ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ህዳር 29 ቀን 2016 ዓ/ም በሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ከተማ በታላቅ ድምቀት ለማክበር በሁሉም አካባቢዎች ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው፡፡