ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል እንግዶች ወደ ከተማዋ እየገቡ ነው

ጅግጅጋ፤ ህዳር 24/2016 (ኢዜአ) ፡- በአገር አቀፍ ደረጃ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለሚከበረው 18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ለመሳተፍ እንግዶች ወደ ከተማዋ እየገቡ ነው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የባህል ቡድን  በበዓሉ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ አመሻሽ ጅግጅጋ ከተማ ገብቷል። 

የባህል ቡድኑ አባላት ጅግጅጋ ከተማ ገራድ ዊልዋል አየር ማረፊያ ሲደርሱ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙስጠፌ አብዲ እና የሶማሌ ክልል የባህል ቡድን አባላት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። 


 

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በትራንስፖርት ለሚመጡ ሌሎች የበዓሉ ተሳታፊዎችም በጅግጅጋ ከተማ መግቢያ በተለምዶ ካራማራ እየተባለ በሚጠራ አካባቢ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል። 

በአገር አቀፍ ደረጃ 18ኛው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ብዝሃነትና እኩልነት ለአገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ ከነገ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

ሕዳር 25 የወንድማማችነት ቀን፣ ሕዳር 26 የብዝሃነት ቀን፣ ሕዳር 27 የአብሮነት ቀን፣ ሕዳር 28 የመደመር ቀን እና ሕዳር 29 የኢትዮጵያ ቀን በሚሉ ስያሜዎች በዓሉ በድምቀት እንደሚከበር ቀደም ሲል መገለጹ የሚታወስ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም