ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስራ ድርጅት አባል መሆኗ ከሰራተኞች መብት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት እድል ፈጥሮላታል - የስራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስራ ድርጅት አባል መሆኗ ከሰራተኞች መብት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት እድል ፈጥሮላታል - የስራና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 24/2016 (ኢዜአ) ፡- ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የስራ ድርጅት አባል መሆኗ ከሰራተኞች መብት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት እድል የፈጠረላት መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።
ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል የሆነችበትን 100ኛ ዓመት በዓል "ማህበራዊ ምክክርና የላቀ ምርታማነት ለማህበራዊ ፍትህ” በሚል መሪ ሀሳብ ሚኒስቴሩ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በተለያዩ ሁነቶች ማክበር ጀምሯል።
ከአከባበሩ በተጓዳኝ ብሔራዊ የአሰሪና ሰራተኛ ጉባኤ እየተካሄደም ይገኛል።
ሁነቶቹ የተዘጋጁት በስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የዓለም ስራ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አሰሪ ፌዴሬሽን ኮንፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ አሰሪዎች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የጋራ ትብብር ነው።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ሀብትን በተቀናጀ መልኩ መምራት፣ የስራ እድል ፈጠራና ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር ላይ ያሉ ፈተናዎች በዘርፉ ላይ የሚፈለገው ለውጥ እንዳይመጣ ማድረጉን ገልጸዋል።
መንግስት በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ማነቆዎችን ለመፍታት የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ነድፎ ወደ ስራ መግባቱን አመልክተዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግና የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የኢንቨስትመንት ድርሻ ማሳደግ መንግስት በዘርፉ ካከናወናቸው የማሻሻያ ስራዎች ይጠቀሳሉ ብለዋል።
በክህሎት የዳበረ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ነው ሚኒስትሯ ያነሱት።
መንግስት ዘላቂ የስራ እድልን ለመፍጠር አሰሪዎች የሚገጥማቸውን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነውም ብለዋል።
የግሉ ዘርፍ በስራው መስክ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አሰግድ ጌታቸው፤ ኢትዮጵያ የዓለም የስራ ድርጅት አባል ከሆነች ጀምሮ በዘርፉ ላይ የተለያዩ ለውጦች መምጣታቸውን አመልክተዋል።
በተለይም ከዓለም አቀፍ የሰራተኞች መብት መከበርና ከሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ጋር በተያያዙ ያሉ ችግሮችን እንዲፈቱ ምቹ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
አገሪቷ ከተቋሙ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና ድጋፍ እንድታገኝ ማስቻሉን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው በዘርፉ ለሚከናወኑ ተግባራት ለማሳለጥ የሚያስችሉ ስምምነቶች መፈጸሟን ገልጸዋል።
የዓለም የስራ ድርጅት (አይኤልኦ) የአፍሪካ ዳይሬክተር ፋንፋን ርዋዩንዶ ካዩራንጋዋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ተቋሙን በመቀላቀል ፈር ቀዳጅ አገር እንደሆነችና የሰራተኞችን መብት ለማረጋገጥ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ፈርማ ስራ ላይ ማዋሏን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰራተኛ አሰራር መስፈርቶችን ለሟሟላት እየወሰደች ያለቻቸውን እርምጃዎችም አድንቀዋል።
በኢትዮጵያ ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ ከባቢን ለመፍጠርና በስራ ላይ የሰራተኞች ደህንነት የተረጋገጠ እንዲሆን የተጀመሩ የጋራ ትብብር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የንግድ ስራ ማህበራት በሰራተኞች መከበር፣ ምቹ የስራ ከባቢን በመፍጠርና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች ላይ ያላቸውን ሚና ማጎልበት እንዳለባቸውም ዳይሬክተሯ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ድርጅቱን የተቀላቀለችበት የ100ኛ ዓመት አከባበርና ብሔራዊ የአሰሪና ሰራተኛ ጉባኤ እስከ ሕዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።
ኢትዮጵያ ከተመሰረተ 104 ዓመት ያስቆጠረውን የዓለም የስራ ድርጅት የተቀላቀለችው እ.አ.አ በ1923 ነበር።