ግንባታው የተጓተተው የጎሬ-ማሻ-ቴፒ መንገድ የመጨረሻ መፍትሔ እንዲሰጠው የአካባቢው ነዋሪዎችና አስተዳዳሪዎች ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
ግንባታው የተጓተተው የጎሬ-ማሻ-ቴፒ መንገድ የመጨረሻ መፍትሔ እንዲሰጠው የአካባቢው ነዋሪዎችና አስተዳዳሪዎች ጠየቁ
ቦንጋ ፤ ህዳር 24/2016 (ኢዜአ)….. ግንባታው በመጓተቱ ምክንያት የተለያየ ችግሮችን እያስከተለ የሚገኘው የጎሬ-ማሻ-ቴፒ መንገድ የመጨረሻ መፍትሔ እንዲሰጠው የአካባቢው ነዋሪዎችና አስተዳደሪዎች ጠየቁ፡፡
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በበኩሉ የመንገዱን ግንባታን ማፋጠን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መንገዱን በመጎብኘት ከአካባቢው ህብረተሰብና ባለድርሻ አካላት ጋር በማሻ ከተማ መክረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች የጎሬ-ማሻ-ቴፒ የመንገድ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን ገልጸዋል።
አቶ ሻወኖ ሻረው የተባሉት የአካባቢው ነዋሪ የአስፋልት መንገድ ግንባታው የዛሬ አራት ዓመት ሲጀመር ተደስተው እንደነበረ ገልጸው መንገዱ በተያለዘት ጊዜ መጠናቀቅ ሲገባው በመዘግየቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው ሰፊ ሃብት ቢኖርም በመንገድ መሰረተ ልማት እጦት ምክንያት የአካባቢው ነዋሪ ተጠቃሚ ባለመሆኑ የዘወትር ቅሬታቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የመንገዱ መጓተት የአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ የማሻ ከተማ ነዋሪ መምህርት ሶፊያ አቢብ ናቸው።
መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ አገልገሎት አለመስጠቱን ተከትሎ የተለያዩ የግብርና ምርቶች ላይ የሚደረገዉ የዋጋ ጭማሪ አቅማቸውን እየተፈታተነ እንደሆነ ተናግረዋል።
መምህርት ሶፊያ አሁን ላይ ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ በመሆኑ የሚመለከተው አካል የመጨረሻ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል ብለዋል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው የመንገዱ መጓተት በህዝቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደርና የቅሬታ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ ያመረተዉን ምርት ገቢያ እንዳያወጣና ሌሎች ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን እንዳያሳልጥ እንቅፋት በመሆኑ የተደረገው ጉብኝትና ውይይት ውጤት የሚያመጣ መሆን አለበት ብለዋል።
በመሆኑም በቀጣይ በተፋጠነ መልኩ የመንገድ ስራውን ለማስጀመር የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንዲሳካ የዞኑ አስተዳደር ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
ከካሳ ክፍያ ጋር ለተያያዙ ችግሮች በተደረሰው ስምምነት መሰረት እልባት በመስጠት ስራው እንዲፋጠን ይሰራልም ብለዋል ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ወይዘሮ እታገኝ እሼቴ እና አቶ አዝመራ አንደሞ አካባቢዉ ከዚህ ቀደም መንገድ የሌለበት በመሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር ላይ ከፍተኛ ጫና እንደነበረ ገልፀዋል።
በለውጡ መንግስት ኦሮሚያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችን በመንገድ ልማት ለማስተሳሰር የተጀመረው የመንገድ ፕሮጀክት በታሰበውና በተያዘለት ጊዜ እየተሰራ አለመሆኑን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የመልካም አስተዳደር ምንጭ የሆነው የመንገድ ፕሮጀክት ችግሮችን በመፍታት ስራውን ለማሳለጥ ከስምምነት በመደረሱ የሚመለከታቸው አካላት በሀላፊነት እንዲሰሩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ክትትሉም እንደሚጠናከር ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ደጀኔ ፍቃዱ ጎሬ-ማሻ-ቴፒ መንገድ ግንባታ በመጓተቱ ምክንያት እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎች ተገቢነት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በአራት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ በ2012 ዓ.ም ግንባታው ቢጀመርም በተለያዩ ምክንያቶች በተፈለገው ልክ ሳይሄድ መቆየቱን ጠቁመው አስተዳደሩ አሁን ላይ የመጨረሻ እልባት ለመስጠት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።
የሚመለከታቸው አካላትን ያቀፈ የጋራ ውይይት መደረጉን ጠቁመው በቀጣይ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ስራው ላይ ለውጥ ለማምጣት መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
በዚህ በተሰጠ ጊዜ ውስጥ ለውጥ የማይመጣ ከሆነ አስተዳደሩ ቀጣይ እርምጃ እንደሚወሰድ ኢንጅነር ደጀኔ ገልፀዋል።
ለመንገዱ መዘግየት ተቋራጩ ካለበት የአቅም ውስንነትና የክትትል ማነስ በተጨማሪ ከወሰን ማስከበርና ካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ክፍተቶችን ለማስተካከል ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የ141 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው መንገዱ ከአራት ዓመታት በፊት በ138 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዞለት ግንባታው መጀመሩ ይታወሳል።