ቀጥታ፡

የጤና ተቋማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል- ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 24/2016 (ኢዜአ)፡- የጤና ተቋማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል የሚደረግ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ።

ምክትል አፈ-ጉባኤዋን ጨምሮ የምክር ቤት አባላት በአዲስ አበባ በጤና ሚኒስቴር ስር እየተከናወኑ ያሉ የጤና ተቋማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲቱዩት፣ አለርት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት እና የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት አገልግሎት በምክር ቤቱ አባላት ተጎብኝተዋል።


 

ከጉብኝቱ በኋላ ምክትል አፈ ጉባዔዋ በሰጡት አስተያየት በተለይ በኢ-ተላላፊ በሽታዎች የሕክምና አገልግሎትን ለማዘመን እና ተደራሽነትን ለማሳደግ ተስፋ ሰጭ ተግባራት እንደተመለከቱ ገልጸዋል።

ከሀገሪቷ የህዝብ ቁጥር እና የህክምና ፍላጎት አንጻር ግን አሁንም በአገልግሎት ተደራሽነት እና አገልግሎት ማዘመን ላይ ይበልጥ መስራት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።

በመዲናዋ በሆስፒታሎች እየተከናወኑ የሚገኙ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ተጠናቀው ወደ ስራ ማስገባት ይገባል ብለዋል።

ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡም ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ፤ የጤና ተቋማት ማስፋፊያ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ ለህክምና ወደ ውጪ የሚደረግ ጉዞን በከፊል እንደሚቀንስ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ለጎረቤት አገራት ዜጎች አገልግሎት በማቅረብ በህክምና ቱሪዝም ረገድ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖራቸውም ጠቁመዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም