ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ አገራት የነበራቸው ጉብኝትና የጉባዔ ተሳትፎ የኢትዮጵያን ክብርና መልካም ገጽታ ከፍ ያደረገ ነው- ዶክተር ለገሰ ቱሉ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ አገራት የነበራቸው ጉብኝትና የጉባዔ ተሳትፎ የኢትዮጵያን ክብርና መልካም ገጽታ ከፍ ያደረገ ነው- ዶክተር ለገሰ ቱሉ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 24/2016 (ኢዜአ)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ አገራት የነበራቸው ጉብኝትና የጉባዔ ተሳትፎ የኢትዮጵያን ክብርና መልካም ገጽታ ከፍ ያደረገ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሣምንት በሦስቱ አገራት የነበራቸውን ቆይታ በማስመልከት የመንግስት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው በኦስትሪያ የቬየና የመንግስታቱ ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጉባዔ፣ በዱባይ 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ የመሪዎች ጉባዔ ተሳትፎ እንዲሁም በቼክ ሪፐብሊክ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
አካታችና ዘላቂ ኢንዱስትሪ ልማት እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል በመከረው በቬየናው የኢንዱስትሪ ልማት ጉባዔ ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት የዘርፉ ስኬታማ ልምዶች የቀረቡበት መሆኑን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያም ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም በመዋቅራዊ እና ሴክተር ማሻሻዎች ረገድ አመርቂ ውጤቶች ማቅረቧን እንዲሁም በተቀናጀ አግሮ ኢንድስትሪን ጨምሮ በርካታ ተሞክሮዎቿን አቅርባ አድናቆት የተቸረችበት እንደሆነም አንስተዋል።
ከ140 ሀገራት መሪዎችና ከ90 ሺህ በላይ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በዱባይ በተካሄደው 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያ ተሞክሮ መቅረቡን ገልጸዋል።
የሀገራት መሪዎች ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር ከተናጠላዊ ይልቅ የተቀናጀ የመፍትሄ እርምጃ ውጤታማ እንደሚያደርግ መግለፃቸውን አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአየር ንብረት ቀውስ ታዳጊ ሀገራት ለሚደረስባቸው ጉዳት የበለጸጉ ሀገራት እንደ ችሮታ ሳይሆን እንደ ግዴታ ወስደው መደገፍ እንደሚገባቸውም በመድረኩ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጋዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በስንዴ ምርታማነት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ የተገኙ አምርቂ ውጤቶች በዘርፉ ተግባራዊ እርምጃን አስቀድማ እያከናወነች መሆኑን ማውሳታቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያን መሰል ስኬታማ ስራ የሰሩ ሀገራት ሊደገፉ እንደሚገባ መናገራቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን አረንጋዴ አሻራ ተሞክሮ በዱባይ በመካነ ርዕይ ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጎ የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች መጎብኘቱን ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎብኝትና የጉባዔ ተሳትፎ የኢትዮጵያን ክብርና መልካም ገጽታ ከፍ ያደረገ እንደነበር አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቼክ ሪፐብሊክ በነበራቸው የስራ ጉብኝት ከሀገሪቱ መሪ ጋር በኢትዮ- ቼክ የሁለትዮሽ ታሪካዊና ነባር ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ መምከራቸውን አንስተዋል።
ከመሪዎች በተጨማሪም ከቼክ ሪፐብሊክ ባለሀብቶች ጋር ውይይቶች ስለማድረጋቸው አስታውሰው፤ በተለያዩ ታሪካዊእና አምራች ኢንዱስትሪዎች ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በደጂታል ኢኮኖሚ በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸው፤ ጉብኝታቸው የተሳካ ነበር ብለዋል።