ኢትዮጵያ አህጉራዊ የፓን-አፍሪካኒዝም የሚዲያ ተቋም እንዲገነባ በትኩረት እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አህጉራዊ የፓን-አፍሪካኒዝም የሚዲያ ተቋም እንዲገነባ በትኩረት እየሰራች ነው
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 24/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አመራር ሰጪነት አህጉራዊ የፓን- አፍሪካኒዝም የሚዲያ ተቋም ለመገንባት በትኩረት እየሰራች መሆኗን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ።
5ኛው የዓለም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጉባኤ በቻይና እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከዘመኑ ጋር ሊራመድ የሚችል አፍሪካ ተኮር የመገናኛ ብዙኃን ለመገንባት ተጨባጭ ሥራዎች እያከናወነች ነው።
አፍሪካዊያን የራሳቸውን እውነት ለዓለም ለማውጣት አንድ አህጉራዊ የፓን አፍሪካ ሚዲያ እንደሚያስፈልግ በመታመኑም ይሄንኑ እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሄንን ችግር ደረጃ በደረጃ ለመፍታትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ልዩ ትኩረት የህዝብ መገናኛ ብዙሃንን አቅም ለማሳደግና የመረጃ ተደራሽነትን ለማጎልበት እንደ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያሉ ተቋማትን አቅም ለማሳደግ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደ አብነት አንስተዋል።
አሁን ላይ የምንኖርባት ዓለም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና በግሎባላይዜሽን በፈጣን የቴክኖሎጂ ለውጥ ላይ መሆኗን ያነሱት አቶ ሰይፈ ይህም የዜጎችን መሠረታዊ ሕይወት በእጅጉ እየቀየረው መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህ አንጻር በቴክኖሎጂ እድገት በተለይም በዲጂታል ሚዲያ የመገናኛ ብዙኃን አውድም በእጅጉ እየተቀየረ መሆኑን ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የእውቀትና የሃሳብ ልውውጥ ለማድረግ አስችሏል፤ በተጨማሪም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ኢኮኖሚውን ለማጠናከርና የቢዝነስ አሠራርን በመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያደረገ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምንም እንኳን ከአገር አገር ልዩነት ቢኖርም በማኅበራዊና በፖለቲካው መስክ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል ብለዋል።
ይሁንና ማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው በተለያዩ አገራት እየተስተዋለ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም በአፍሪካ ውስጣዊ ግጭቶችን ለማባባስና በማኅበረሰቦች መካከል ክፍፍል ለመፍጠር አስቻይ ምህዳር ሆኗል ነው ያሉት።
ከዚህ አንጻር፤ ኢትዮጵያም የዚህ ችግር ሰለባ መሆኗን አንስተዋል።
በመሆኑም ፎረሙ በተለይም የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ከአዲሱ ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ሰው ሠራሽ አስተውሎት(አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ)ን ጨምሮ እያደገ የመጣውን ይህን ተግዳሮት እንዴት ማቃለልና የሰዎችን ሕይወት በአዎንታዊ መልኩ እንዴት መቀየር እንደሚገባ መፍትሔ ማመላከት አለበት ብለዋል።
ጎን ለጎንም በዚህ ዓለም ብሪክስን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች አማራጭ የሚዲያ ትርክት መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም አሁን ላይ አሉታዊ የሚዲያ ትርክትን ለመግታትና የጋራ ብልፅግናን ማምጣት የሚያስችል የወል ትርክት መገንባት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ሚዲያው ትርክቱን የሚፈጥረው በአብዛኛው የተሳሳቱ መረጃዎችና አሳሳች ይዘቶችን በመጨመር መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት አፍሪካን በተመለከተ የሚያቀርቡት አሉታዊ ዘገባን መመልከት በቂ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት በተለይም በቴክኖሎጂ ትልቅ አቅም እየፈጠሩ ያሉ አገራት ለአብነትም ቻይና የጋራ ትርክት በመፍጠር ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያመጣ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጠንሳሽነት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በማስጀመር እስካሁን 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ መትከሏን ገልፀዋል።
"ይሁንና የዓለም አቀፍ ሚዲያ ትርክቶች ይህንን ዓይነቱን ስኬታማ የአፍሪካ ተሞክሮ ሸፍኖታል" ሲሉ ተናግረዋል።
አብዛኛው የዲጂታል ሚዲያዎች አሉታዊ ነገሮችን ለማስፋትና ጥፋት ሊያስከትሉ የሚችሉ ግጭትን መሠረት ያደረጉ ዘገባዎች እንዲበዙ ትልቅ አስተዋጽዖ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከፍተኛ የሪፎርም ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
"እንደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሚዲያ ሽፋንን ከግምት በማስገባትና እንዲሁም የተቋሙን አገልግሎት ለማዘመንና ዲጂታላይዜሽንን በማስፋት ጥራት ያለው የሚዲያ የይዘት ሥራዎችን ለማቅረብ አሁን ላይ እጅግ ዘመናዊ የኤዲቲንግና የድምፅ ቅጅ መሳሪያዎች የተተከሉለት ሦስት የቴሌቪዥን ስቱዲዮና አራት የሬዲዮ ስቱዲዮችን ያቀፈ የሚዲያ ኮምፕሌክስ አለው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተነሳሽነት መሠረት በማድረግ አህጉራዊ የፓን አፍሪካ ሚዲያ ለማቋቋም ትኩረት አድርጋለች ሲሉም አክለዋል አቶ ሰይፈ።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአፍሪካን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ሥራ ለመሥራትና የመሪነት ሚናውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።