ቀጥታ፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል ያከናወናቸውን ተግባራት ተመለከተ

ሀዋሳ ፤ ህዳር 24/2016 (ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል ያከናወናቸውን ተግባራት ተመልክቷል።

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ኮሚሽኑ በሲዳማ ክልል በተሳታፊ ልየታና በሌሎች የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ላይ ያከናወናቸውን ተግባራት ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል።

አቶ ጥበቡ በሪፖርታቸው እንደጠቀሱት በክልሉ በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ ተወካዮችን በመወከልና በአጀንዳ ልየታ ሥራዎች ከ20ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ብለዋል።

በዚህም ከሁሉም ወረዳዎችና ከተሞች ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከ800 በላይ የሚሆኑ ተወካይ ተሳታፊዎች መመረጣቸውን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባልና የቡድኑ አስተባባሪ ወይዘሮ አቡኔ ዓለም እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ እንደሀገር ላሉብን ችግሮች ምክንያት የሆኑ ልዩነቶችን በማጥበብ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ኮሚሽኑ የተሰጠውን ተልዕኮ እንዲወጣ ድጋፍ ያደርጋል።

ለዚህም ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዕሴቶቻችንን በመጠቀም እያከናወነ ያለውን ተግባር እንዲያጠናክር በተለይም በዝግጅት ምዕራፎች የሁሉም ዜጋ ተሳትፎና አካታችነት የማረጋገጥ ስራ እየሰራ መሆኑን በበጎነት አንስተዋል።

በምልከታውም የውክልና ሂደት እና ቋንቋን ተርጉሞ በመጠቀም ማህበረሰብን ተደራሽ ለማድረግ የተሄደበትን ርቀት እንደሚያረጋግጥም ማሳያ ነው ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በሀዋሳ በሚኖረው ቆይታ ከክልሉ መንግስት አማካሪ፣ ከክልሉ የኮሚሽኑ ተባባሪ አካላትና ከተመረጡ የወረዳ ተባባሪ አካላት ጋር እንደሚወያይም ተገልጿል።

እንዲሁም በተመረጡ ወረዳዎች በውይይትና በምርጫ ከተሳተፉ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር እና ከወረዳዎቹ ነዋሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ የማጠቃለያ ግብረ መልስ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም