ቀጥታ፡

ለዜጎች የምትመች ሀገር ለመፍጠርና የማህበረሰብ ለውጥ ለማምጣት የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ማስፋፋት ይገባል

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 24/2016 (ኢዜአ) ፦ ለዜጎች የምትመች ሀገር ለመፍጠርና የማህበረሰብ ለውጥ ለማምጣት የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ማስፋፋት እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ተናገሩ።

የኮርያ ሪፐብሊክ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ቢሮ ያዘጋጀው ዓለም አቀፉ የበጎ ፍቃደኞች ቀን በአዲስ አበባ ተከብሯል።

ቀኑ “የእያንዳንዱ ሰው የበጎ ፍቃድ ተሳትፎ ድምር ውጤት ሃያልነት” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከበረው።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ለዜጎች የምትመች ሀገር ለመፍጠርና የማህበረሰብ ለውጥ ለማምጣት የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ማስፋፋት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያንና የኮርያ ሪፐብሊክን የቆየ ወዳጅነት ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ በበጎ ፍቃድ ስራ ዓለም አቀፋዊ ትብብር በመፍጠር ዓለምን ለሰው ልጆች የምትመች ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል።

ሁሉም ሰው በእውቀቱ፣ በሙያው ወይም በገንዘቡ የሚችለውን ያክል የበጎ ፍቃድ ስራ ቢሰራ የማይፈታ የማህበረሰብ ችግር እንደማይኖርም አብራርተዋል።


 

የኮርያ ሪፐብሊክ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዲዮግ ቾ በበኩላቸው ቀኑ በጎ ፍቃደኞች ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን አውጥተው ለማህበረሰብ ለውጥ ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅናና ምስጋና ለመስጠት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ባለፈው አመት 21.9 ሚሊየን በጎ ፍቃደኞች ለ53 ሚሊየን ሰዎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት 17 ቢሊየን ብር የሚገመት ወጪ ማዳን መቻሉን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም