የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዝሃነትን በእኩልነት በሚያስተናገድ መልኩ መቃኘት አለበት- ዶክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዝሃነትን በእኩልነት በሚያስተናገድ መልኩ መቃኘት አለበት- ዶክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 24/2016 (ኢዜአ) ፡-በኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ብዝሃነትን በእኩልነት የሚያስተናገድ የፖለቲካ ቅኝትን መፍጠር እንደሚገባ የህገመንግስትና የፌደራሊዝም አስተምህሮ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ ገለጹ።
18ኛ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል ከነገ ጀምሮ በጅግጅጋ ከተማ ለአምስት ተከታታይ ቀናት "ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ይከበራል።
አምስቱ ቀናትም ኅዳር 25 የወንድማማችነት፣ ኅዳር 26 የብዝኀነት፣ ኅዳር 27 የአብሮነት፣ ኅዳር 28 የመደመር ቀን እንዲሁም ኅዳር 29 ደግሞ የኢትዮጵያ ቀን በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራሉ፡፡
በዚሁ ጉዳይ ላይ የህገመንግስትና የፌደራሊዝም አስተምህሮ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለኢየሱስ፤ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በማብራሪያቸው ባለፉት ዓመታት የተከበሩት የብሔረሰቦች ቀን በዓላት ብዝሃነትን ለሀገራዊ አንድነት ማጠናከሪያ ከመሆን ይልቅ ልዩነትን የሚያሰፉ አጀንዳዎች ይንጸባረቁባቸው እንደነበር ጠቅሰዋል።
ሆኖም ከ15ኛው የብሔረሰቦች ቀን ወዲህ ለሀገራዊ አንድነት መጠናከር የተሻለ አጋጣሚ አድርጎ ለመጠቀም ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የብዝሃነት ሀገር መሆኗ የሚታወቅ ቢሆንም ብዝሃነትን በእኩልነት የሚስተናገድ ስርዓት ሳይገነባ መዝለቁን አንስተዋል።
ቀደም ሲል የነበረው የፖለቲካ ምህዳር ብዝሃነት የልዩነት መፍጠሪያ የማድረግ እንጂ ለሀገራዊ አንድነት ማጠናከሪያ እንዲሆን አላደረገም ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያን በትክክል የሚገልፅና ወደፊት የሚያሻግር፣ ብዝሃነትን በእኩልነትና በፍትሐዊ ውክልና ማስተናገድ የሚያስችል የፖለቲካ ቅኝት መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የበለፀገች፣ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ብዝሃንትን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋልም ብለዋል።
ሕዝቦች ለረዥም ዘመናት ይዘውት የቆዩትን አብሮነት በማጽናት ከልዩነት ይልቅ አንድነት እንዲያጎለብቱና በሕገ መንግሥቱና በህብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ስርዓቱ ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እርስ በርስ መተዋወቂያ፣ የባህል መድመቂያ መድረክ ከመሆኑ ባለፈ፤ ለሀገራዊ አንድነት የሚያጠናክሩ አዳዲስ ዕይታዎች ላይ ውይይት በማድረግ መፍትሔ የሚቀርብበት አውድ እንዲሆንም መስራት ይጠይቃል ብለዋል።