ቀጥታ፡

ሪፖርተር ጋዜጣ በሕዳር 23 ዕትሙ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜና በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ አቅዷል በሚል የሰራው ዘገባ ሐሰተኛና አሳሳች ነው - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 24/2016 (ኢዜአ) ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ በሕዳር 23 ዕትሙ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜና በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ አቅዷል በሚል የሰራው ዘገባ ሐሰተኛና አሳሳች ነው ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ጉዳዩን በሚመለከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መግለጫ አውጥቷል።

የመግለጫው ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል ፦

የሪፖርተር የአማርኛ ጋዜጣ በህዳር 23/2016 እትሙ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ከአንድ የፓርላማ አባል ቀረበ ከተባለ አስተያየት ላይ ተነስቶ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜና በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ ማቀዱን በማስመልከት ያወጣው ዘገባ ፈጽሞ ሐሰተኛና አሳሳች ከጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር ያፈነገጠ ድርጊት ሆኖ አግኝተነዋል።

በመሆኑም ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በተመለከተ የቀረበ ዕቅድ ካለመኖሩም ባሻገር እስከ አራት ሰዓት በፈጀው ውይይት ወቅት በብሔራዊ ባንክ የተነገረ ነገር እንደሌለ ህብረተሰቡ ተረድቶ ከዚህ አይነት አሳሳች መረጃ እንዲጠበቅ፣ የሪፖርተር ጋዜጣውም በሚቀጥለው እትሙ ይህንኑ የሐሰት ዘገባ እንዲያርም እየጠየቅን፣ በዚህ አሳሳች ዘገባና አሉባልታ ምክንያት በዋጋ ላይ የሚፈጠር ማንኛውም ሰው ሰራሽ ጭማሪ ተቀባይነት እንደማይኖረውና ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ ለማሳሰብ እንወዳለን።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም